Tuesday, January 10, 2023

አማራ የኢትዮጵያዊነት ርዕዮተ ዓለም ስም ነው።




=> ኢትዮጵያ፡ ስለዐምሐራነት ስትፋረድ! <= ልብ ያለው ልብ ይበል የሚሰማ ጆሮ ያለው፡ መስማትን፡ ይስማ! 

(በንቡረ እድ ኤርምያስ ከበደ ወልደኢየሱስ)
================
.
"ኢትዮጵያዊነት" ከሚለው ቃል ጋር፡ የጥሬ ዘርና የምሥጢር ÷ የዘይቤና የትርጉም ተዘምዶ ያላቸው፡ በዓለም ህዝቦችና ቋንቋዎች ዘንድ የታወቁ ፡ አንዳንድ ይፋ ቃላት አሉ፡፡  ከእነዚህ መካከል፡ ... "ዐምሐራነት"  የሚለው የውህደት ስም አንዱ ነው፡፡ ከ"ኢትዮጵያ" ጋር የተዛምዶ ግንኙነት አላቸዉ ከተባሉት ቃላት መካከል፣ በመጨረሻ የተወሳው፡ "ዐምሐራ" የሚለው መጠሪያ ቃል፡ ለተነሣንበት አርእስት፡ የበለጠ አግባብነት አለው፡፡

የዚህም መክንያት፣ ኢትዮጵያ የቆመችለትን እምነት የሚጻረሩ አንዳንድ ባዕዳንና የአገር ተወላጆች፡ በዛሬው ዘመን ÷ በቅርቡም፡ እስካለፈው ምዕት ዓመት ድረስ፡ በሕዝቡና በአገሪቱ ላይ ሊጭኑ ያቀዱትን፡ የየራሳቸውን የገዢነት ቀምበርና የግል ፍላጎታቸዉን ዓላማ እዉን ለማድረግ ሲሉ፡ ስለዚሁ፡ "ዐምሐራ" ስለሚለው አገር-አቀፍ ስያሜ፡ ኾን ብለዉ የፈጠሩት፡ እጅግ የረቀቀ÷ የስሕተትና የቅራኔ ትርጓሜ ስላለ ነዉ፡፡  ስለዚህ፡ እዚህ ላይ የተለየ ትኲረት ተሰጥቶት፡ የቃሉን ምንጭና እዉነተኛ ትርጉም በሚመለከት፡ በቂ መስረጃዎችን ከማቅረብ ጋር፡ አጠር፡ ባለ ሐተታ፡ ስለቃሉ ዓቢይ ቁም ነገር፡ መተንተንና ማብራራት፡ ግዴታ ይኾናል፡፡ "ዐምሐራ" የሚለዉ ቃል፡ መልእክትና ትርጉም ባለው ምክንያት፡ በኢትዮጵያ ምድር ለሚኖረው፡ ለአብዛኛው የአገሪቱ ነባር ሕዝብ የተሰጠ ትዉፊታዊ ስያሜ ነዉ፡፡

ቃሉ፡ ከግእዝ ተገኝቷል፡፡ በግእዝ፡ "ዐም" ማለት፡ "ሕዝብ" ÷ "ሐራ" ማለት ደግሞ፡ "ነጻ" ማለት ነዉ፡፡ ስለዚህ "ዐምሐራ" የሚለው ስያሜ፡ የቃል ለቃል ትርጉሙ፡ "ነጻ ሕዝብ" ማለት ሲኾን፡ ይህም ትርጉም፡ የእዉነተኛ ኢትዮጵያዊን ማንነት ከሚገልጹት ዓበይት ባሕርያት መካከል፡ አንዱ መኾኑን በግልጽ ያመለክታል፡፡ ግእዝ፡ ራሱን የቻለ፡ ፊደል ያለዉ፡ የኢትዮጵያዉያን፡ የመጀመርያዉ እናት ቋንቋቸው መኾኑ፡ በዓለም ሕዝቦች ዘንድ ሳይቀር፡ በይፋ የታኸቀ ነው፡፡ (ግእዝ፡ በዓለም ተመሳሳይና ወደር የሌለው ÷ ራሱን የቻለና የራሱ የኾነ ፊደል ያለዉ፡ የኢትዮጵያዉያን፡ መሠረታዊ (ግንድ) ቋንቋቸው ነዉ፡፡ ባሁኑ ጊዜ፡ በተወሰኑ የሕዝቡ ወገኖች ዘንድ መነጋገሪያ ልሳናቸው÷ በመላው ሕዝቡ ዘንድ ግን፡ የሃይማኖትና የአምልኮ ቋንቋቸው አድርገው የሚጠቀሙበት ሲኾን፡ የማንነታቸው መታወቂያ ለኾነዉ ለቅዱሱ ኪዳን ዉርሳቸዉ መዘገብ÷ በእርሱ ላይ ለተመሠረተው የትምህርት እና የእውቀት ፈለጋቸዉ ደግሞ፡ የማያቋርጥ ምንጫቸው ኾኖ ኖርዋል፡ ዛሬም ይገኛል፡፡

የስሙ ትርጓሜ እንደሚያመለክተውና እዉነተኞች የቋንቋ ሊቃዉንት እንዳረጋገጡት፡ አዳምና ሔዋን ይነጋገሩበት የነበረዉ፡ ቀዳማዊዉ፡ የቅዱሱ ኪዳን ልሳን መኾኑ ስለታመነበት፡ ዕድሜው፡ ወደኋላ፡ ወደመጀመሪያው ዓመተ ዓለም ዘልቆ የሚኼድ ኾናል፡፡ የዐምሐራዉ ኅበረተሰብ፡ መነጋገሪያዉ ያደረገው ቋንቋ፡ "ዐምሐርኛ" ተብሏል፡፡ የዚህ ኀብረተሰብ፡ የቃል ብቻ ሳይኾን፡ የጽሕፈት መገናኛዉ ጭምር የኾነዉ፡ ይህ ልሳን፡ ግንዱ፡ ግእዝ ቢኾንም፡ በጋብቻና በልደት እንደተዋሃደዉ፡ እንደቋንቋዉ ባለቤት ኹሉ፡ ዐምሐርኛም፡ ብሔር-አቀፍ ኾኖ፡ በአገሪቱ ዉስጥ በሚነገሩት፡ አያሌና የተለያዩ በኾኑ ልሳናት፡ ራሱን ሲያበለጽግ የኖረ ቋንቋ መኾኑ፡ የቃላቱ ቤተ መዛግብት ያረጋግጣል ፡፡

"ዐምሐራ" የሚለው ስም፡ ለምሳሌ ፡ አገዉ÷ አርጎባ÷ አፋር ÷ ኦሮሞ÷ ጉራጌ÷ ጋፋት÷ ሐዲያ÷ ወላይታ÷ ከምባታ÷ ኲናማ÷ ወይም ትግሬ እንደሚባሉት፡ በየጎጣቸዉና በየክልላቸው÷ በየእምነታቸውና በየቋንቋቸዉ፡ ተለያይተዉና ተወስነዉ፡ በየስማቸዉ እንደሚታወቁት ብሔሮች÷ ወይም፡ ሴማዉያን÷ ካማውያንና ያፌታዉያን ተብለው፡ በመላዋ ምድር ተሠራጭተው እንደሚኖሩት፡ እንደሥስቱ የሰዉ ዘር፡ የትውልድ ቅርንጫፎች፡ ይህም ኅብረተሰብ፡ "አንድ ነጠላ ጎሣ ወይም ነገድ ነዉ" ተብሎ፡ ለእርሱ፡ መለያና መታወቂያ ይኾን ዘንድ የተሰጠ ስያሜ አይደለም፡፡ በሌላ አገላለጽ፡ ዐምሐራ፡ የአንድ ጎሣ ወይም የአንድ ነገድ ወይም የአንድ ዘር ወገን አይደለም ማለት ነው፡፡ የቃሉ ፍቺ እንደሚያመለክተዉ፡ ዐምሐራ፡ በኢትዮጵያ ምድር የሠፈሩ÷ ከተለያዩ ጎሣዎች÷ ነገዶች÷ ዘሮች÷ ቋንቋዎች÷ ባህሎች እና/ወይም ሃይማኖቶች የተዉጣጡ ወንዶችና ሴቶች፡ እርስ በርሳቸው በመጋባት፡ በሥጋ፡ አንድ የኾኑበት ህልውና ነዉ፤ በመንፈስም፡ ቀድሞ፡ በኪዳነ ልቦና÷ ቀጥሎ፡ በኪዳነ ኦሪት÷ በመጨረሻ፡ በኪዳነ ምሕረት ፡ የክርስትና ተዋህዶ ሃይማኖት፡ ከእግዚአብሔር በመወለድ፡ ሥጋቸዉና ነፍሳቸዉ÷ እነርሱም፡ ኹላቸዉ፡ በአንዱ መንፈስ ቅዱስ፡ ፍጹም አንድ የኾኑበት ሕይወት ነዉ፤ በአጠቃላይ፡ "ኢትዮጵያዊነት" የተባለዉን፡ ዘለዓለማዊ የህልውና ዓላማ፡ በሕያዉነት ከግብ ለማድረስ፡ መለኮታዊዉን ጥሪ፡ በፍቃዳቸው ተቀብለው፡ ለእርሱ፡ በጋራ፡ ቃል ኪዳን የገቡና ለሰውም ኾነ ለዲያብሎስ ተገዢ ከመኾን ነጻ ወጥተው፡ በእግዚአብሔር ሕገ መንግሥት፡ በእኩልነት ፍትሕ በመመራት እየተዳደሩ፡ እንደአንድ ቤተሰብ የሚኖሩበት ሥርዓተ ሀገር ነዉ፡፡

ዐምሐራዉ፡ ከላይ እንደተገለጸዉ፡ የእንያ፡ እያንዳንዳቸው፡ የየግላቸዉን ብሔረኝነትና ጎሠኛነት÷ አምልኮና ልሳን በፈቃዳቸው ትተዉ፡ ኢትዮጵያዊነትን ከፍጹም ኹለንተናዉ ጋር፡ በፈቃዳቸውና በሃይማኖት የተቀበሉ፡ የኢትዮጵያ ጥንታዉያን ባላገሮች ኅብረተሰብ ስለኾነ፡ ቀጥሎ ባለዉ ሐተታ እንደሚብራራዉ፡ ይህ ኅብረተሰብ፡ እውነተኛው ኢትየጵያዊ ኾኖ ለመገኘት በቅቷል፡፡ እንግዲህ፡ ማንኛዉም ግለሰብ፡ ወንድ ኾነ ሴት፡ በዚህ ኢትዮጵያዊነት አምኖ፡ የዚህ ኅብረተሰብ አባል ለመኾን፡ በፍጹም ነጻነት ፈቃደኛ ሲኾን፡ የሚፈጸምለት ሥርዓት አለ፤ ይኸዉም፡ ከመንፈስ ቅዱስ በመወለድ፡ በእግዚአብሔር መንግሥት ዉስጥ፡ ለአዲሱ ኪዳን ማኅበራዊ ሕይወት የሚያበቃዉን ጸጋ የሚጎናጸፍበት ልዩ ሥርዓት ነው፤ እርሱም፡ በሃይማኖት እዉቀት÷ በእዉነተኛ ንስሓ÷ በክርስትና ጥምቀትና በቅዱስ ቁርባን ምሥጢራት ይፈጸማል፡፡ ለዚያ ግለሰብ፡ይህ ሥርዓት እንደተፈጸመለት "ዐምሐራ ኾነ!" ይባላል፤ "ክርስቲያን ኾነ!" ወይም "ኢትዮጵያዊ ኾነ!" ማለት ነዉ፡፡ "ዐምሐራነት"፡ ኋላ፡ በሥጋ ጋብቻ ጭምር እስኪዋሃዱበት ድረስ፡ በቅድሚያ፡ እንዲህ በመንፈስ የሚወለዱበት ስለ ኾነ፡ ጎሣ ወይም ብሔር አለመኾኑ፡ በዚህ ይታወቃል፡፡ በዚህ ጊዜ፡ ያግሰብ፡ ኢትዮጵያዊነት፡ በሚያስተማምን ቃል ኪዳን፡ ለዘለዓለም የሚያጎናፅፈውን፡ ያን፡ በመለኮታዊ ጸጋ የተገኘውን ሰብአዊ ነጻነት እንዳይቀዳጅ፡ ከልክሎት ከኖረዉ፡ ከጠባብ ብሔረኝነትና ከጎሠኝነት÷ ከቋንቋና አምልኮ ባዕድ ቁራኝነት÷ ከአጓጉል አስተሳሰብም ቀምበር ተላቅቆ፡ የእውቀት ብርሃን የወጣለትና የነጻነትን አክሊል የተቀዳጀው ኅብረተሰብ አባል ለመኾን የበቃ የይኾናል፡፡

ይህ "ዐምሐራ" የመኾን ምሥጢር፡ "ኢትዮጵያዊ" ከመኾን ጋር የሚመሳሰልና እንደ "ኢትዮጵያዊነት" ኸሉ፡ ያልተቋረጠ ትንግርታዊ ሂደት ያለዉ ኾኖ ኖርዋል፡፡ "ዐምሐራ ኾነ!" ማለት፡ ከላይ እንደተወሳዉ፡ " ኢትዮጵያዊ ኾነ" እንደማለት ብቻ ማለት ሳይኾን፡ በአሁኑ ግዜ፡ በፍጥረተ ዓለሙ ዘንድ፡ በይበልጥ እውቅና እንዳገኘዉና በመጨረሻው ዘመን፡ የሰውን ዘር እንደገና አዋህዶ፡ ፈጹም አንድ እንደሚያደርገው ፡ እንደ አዲስ ኪዳኑ ስያሜ "ክርስቲያን ኾነ" ማለትም ነዉ፡፡ በዚህ መሠረት፡ ዐይነተኛዉ ማለት አማናዊው (እውነተኛው) የዐምሐራዉ ኅብረተሰብ፡ ኢትዮጵያ፡ በእግዚአብሔር መንግሥትነት ሥር ተዋህዳ የኖረች፡ የማትከፋፈል፡ አንዲት አካል መኾኗን በማመን፡ በጎሣ ወይም በዘር መለያየትን የሚቃወም በመኾኑ ነው፡፡ እንዲያዉም፡ ኢትዮጵያዊነት፡ ከዚህ የበለጠ፡ የመጠቀና የጠለቀ÷ የሰፋም ባሕሪ አለዉ፤ ይኸውም፡ ለኢትዮጵያ፡ አንዱሁም፡ ላለፉትና ለዛሬዎቹ÷ ለወደፊቶቹም ኢትየጵያዊያንና ኢትዮጵያዊያት ብቻ ተለይቶና ተወስኖ የተሰጠ÷ እየተሰጠ ያለና የሚሰጥም አለመኾኑ ነው፤ ነገር ግን፡ በዘመነ ሐዲስ ኪዳን፡ ሞክሼዉ (መሰሉ) አንደኾነዉ፡ እንደ ክርስቲያንነት ኹሉ የሰዉ ዘር በመላ ተጠቃልሎና በመለኮታዊዉ መንግሥት ሥር ተዋህዶ፡ አንድ እንዲኾንበት፡ አግዚአብሔር አምላክ፡ ለፍጥረተዓለሙ ደህንነትና መልካም ሕይወት፡ አዘጋጅቶ የዘረጋዉ ዘላለማዊ ዕቅድ ነው እንጂ፡፡ ይህም፡ በምድር ላይ ላለው፡ ለሰው ልጆች ችግር ኹሉ፡ የመጨረሻዉ መፍትሔ አንደሚኾን ይታመናል፡፡ ከዚህ የተነሣ፡ ባንድ ወገን፡ "መላዉ ዐማራ" በሚል ስያሜ የተቋቋመው ድርጅት፡ በዉስጡ፡ "ዐማራ" ከሚያሰኘዉ፡ ከቅዱሱ ኪዳን ተዋህዶ ሃይማኖት ዉጪ የኾኑትን ግለሰቦች ጭምር፡ በአባልነት አጠቃልሎ እንዲይዝ በማድረግ÷ በሌላው ወገን ደግሞ፡ በአገር- አቀፍ ደረጃ፡ "የዐ(አ)ማራው ክልል " በሚል ዕቅድ፡ የተጀመረውን የመከፋፈል ዓላማ ከግብ ለማድረስ በመሞከር፡ የሚፈጸመው ድርጊት፡ በየመልኩ ሊወገዝ የይገባዋል፡፡ ምክንያቱም፡ ይህ፡ በኹለቱ ወገኖች የሚፈጸመው ድርጊት፡ ዐምሐራን፡ ከመሠረታዊው፡ የኢትዮጵዊነት ባሕርዩ አዉጥተዉ፡ እንደጎሣ ለማስቆጠር፡ የኢትዮጵያ የደም ጠላቶች በሚያውጠነጥኑት ሴራና በሚያካኼዱት ዘመቻ ውስጥ ተባባሪ÷ ደጋፊና መሣሪያ መኾንን፡ በግልጽ አረጋግጦ የሚያሣይ፡ የክህደትና የዓመፅ ተግባር በመኾኑ ነው፡፡

ስለዚህ "ዐምሐራ"፡ ኢትዮጵያዊነትን ሕያው ለማድረግ፡ ለመጠበቅና ለማስፋፋት፡ ቃል ኪዳን የገባ "ክርስቲያን" ማለት ስለኾነ ከላይ የተመለከተውን፡ በድርጅቱም ኾነ በብሔራዊው ደረጃ የሚታየውን የተዛባ አሠራር፡ ጉዳዩ የሚመለከታቸዉ ወገኖቼ ኹሉ፡ በብርቱ አስበውበት፡ እራሳቸውን በንሰሓ÷ ድርጊታቸውንም፡ በእውነተኛ ኢትዮጵያዊነት ማስተካከልና ማብቃት ይኖርባቸዋል፡፡

✞ ✞ ✞ ✞ ✞ ✞ ✞

በንቡረ እድ ኤርምያስ ከበደ ወልደኢየሱስ