Tuesday, November 22, 2022

November 20, 2022. ‹‹የእኛ ብሔርተኝነት የበሰለና ዴሞክራሲያዊ ነው›› አቶ በቴ ኡርጌሳ፣ የኦነግ የፖለቲካ ኦፊሰርቆይታ Reporter :by Yonas Amare.



ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በባዮሎጂ፣ ከወለጋ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ፣ ከአርሲ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ማስተርስ ኦፍ ቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን፣ እንዲሁም ከኒው ጄኔሬሽን ዩኒቨርሲቲ በሄልዝ ኦፊሰርነት ተመርቀዋል፡፡ ገና ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሳሉ በኦሮሞ ተማሪዎች ማኅበር ውስጥ ይንቀሳቀሱ እንደነበር የሚናገሩት አቶ በቴ ኡርጌሳ ሥርዓቱ የፖለቲካ ጥያቄ የሚያነሱ ሰዎችን የማይታገስ ስለነበር በጊዜው እስራት እንደገጠማቸው ይናገራሉ፡፡ ይህ ሁኔታ በዩኒቨርሲቲ ከሚንቀሳቀሱ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ተማሪዎች ጋር የበለጠ እንዲቀራረቡ፣ ከዚያም ወደ ፖለቲካ ትግል ለመግባት እንዲወስኑ እንዳደረጋቸው ይናገራሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት የኦነግ የፖለቲካ ኦፊሰር የሆኑት አቶ በቴ ድርጅታቸው በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ ከስደት ቢመለስም፣ ነገር ግን በሚደርስበት ከፍተኛ ጫና መደበኛ ሥራውን ለመሥራት መቸገሩን ይናገራሉ፡፡ ፓርቲያቸው ኦነግ ሌሎች ሕዝቦችን በጠላትነት የማይፈርጅ፣ የጠራና የበሰለ የፖለቲካ መስመር እንደሚከተል የሚናገሩት አቶ በቴ፣ ከፓርቲያቸው ጉዳይ ባሻገር በቅርብ ጊዜ እየተባባሰ ስለመጣው የኦሮሚያ ቀውስና ስለኦሮሞ የፖለቲካ ትግል ከዮናስ አማረ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- የኦሮሞ የፖለቲካ ጥያቄ ምንድነው?

አቶ በቴ፡- ኦሮሞ ጥያቄ ሳይሆን የፖለቲካ ፍላጎት ነው ያለው፡፡ ጥያቄ ከሆነ የሚመልስ አካል አለ ማለት ነው፡፡ ኦሮሞ ግን ማግኘት የሚፈልጋቸው የፖለቲካ ፍላጎቶች ናቸው ያሉት፡፡ የአቢሲኒያ ኢምፓየር ሲስፋፋ ኦሮሞና የሌሎች ሕዝቦች ፖለቲካዊ ፍላጎት በኃይል ተደፍጥጦ ቆይቷል፡፡ የአቢሲኒያ ኢምፓየር መስፋፋት አፋኝና ጨፍጫፊ ስለነበር፣ በተለያዩ የኦሮሚያ ክፍሎች ተቃውሞና ትግል ይካሄድ ነበር፡፡ የሜጫና ቱለማ እንቅስቃሴም ሆነ የኦነግ እንደ ድርጅት መመሥረት የዚያ ሒደት ውጤት ነው፡፡ የኦሮሞን የፖለቲካ ፍላጎት ወይም ጥያቄ ሕዝቡ ያነሳው እንጂ ኦነግ አልፈጠረውም፡፡ ኦነግ ጥያቄውን ተመርኩዞ፣ የፖለቲካ ፕሮግራም ቀርፆና ተደራጅቶ አታግሏል፡፡ ኦነግ የተለያዩ የኦሮሞ ብሔርተኞችን በአንድ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ወይም መስመር እንዲታገሉ በማድረግ የመጀመሪያው ድርጅት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች አልነበሩም ወይ? በርካታ የኦሮሞ ወጣቶች እንደ መኢሶን (የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስታዊ ንቅቃቄ) ባሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ ገብተው ሲታገሉ አልነበረም ወይ?

አቶ በቴ፡- ኦሮሞዎችማ በብዙ የፖለቲካ አሠላለፎች ውስጥ ነበሩ፡፡ አፋኝ ብዬ ባስቀመጥኩት ሥርዓት ውስጥም እኮ ኦሮሞዎች ነበሩ፡፡ ኦሮሞዎች ከምኒልክ ጋርም ነበሩ፡፡ እነ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴና ባልቻ አባ ነፍሶም የምኒልክ አንጋሾች ነበሩ፡፡ ነገር ግን እነርሱም ቢሆኑ በአቢሲኒያ ኢምፓየር መስፋፋት ሰለባ የሆኑና የተማረኩ ነበሩ፡፡ ሥርዓቱን ተቀብለውና በዚያ ውስጥ አድገው ለሥርዓቱ ሲያገለግሉ የኖሩ ናቸው፡፡የኦሮሞ ሰው በዚህም በዚያም ውስጥ አለና ያ ሥርዓት የኦሮሞ ማኅበረሰብን ይወክላል የሚሉ ሰዎች ተሳስተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ ኦሮሞ ሁለት ሚና ነበረው፣ ገዥም ተገዥም ነበር ብለው የሚከራከሩ ወገኖች አሉ፣ እኛ ይህንን እንቃወማለን፡፡ አንድን የፖለቲካ ሥርዓት ያንተ የሚያደርገው መሠረታዊ የሆኑ የአንድን ኅብረተሰብ እሴቶችን ሲወክል ነው፡፡ የግለሰብ በአንድ የፖለቲካ ማኅበር መግባት፣ ማንነቱን አጥቶና ገብሮ ለሥርዓቱ መታገሉ አይደለም ያን ሥርዓት ያንተ የሚያደርገው፡፡ ያ ሥርዓት በአንተ ውቅር፣ ማንነትና ባህል የተቀረፀ በመሆኑ ነው አንተን የሚወክል ሥርዓት ነው የሚባለው፡፡

የአቢሲኒያ ሥርዓት በአፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ መንግሥት የተባለው፡፡ ይህ ሥርዓት ደግሞ በዋናነት መገለጫዎቹ በዋናነት ኦማርኛ ተናጋሪነት፣ የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን የመንግሥት እምነት አድርጎ የያዘ፣ በዘር ወይም በደም ሥልጣን የሚወራረስ ሥርወ መንግሥት ነው፡፡ አማርኛ ተናጋሪ ሲባል ሥርዓቱ የአማራ ነው ለማለት አይደለም፡፡ በሥርዓቱ ውስጥ አማራ ስለመኖሩ እኛ አናውቅም፡፡ እንዲህ ያደረገው የአማራ ብሔረሰብ ነው ብለን ጠቅሰን አናውቅም፡፡ ሥርዓቱም የአማራ ነው አላልንም፡፡ ነገር ግን ሥርዓቱ ሌሎች የቋንቋ ቤተሰቦችን የጨቆነና እንዲቀሩ ያደረገና በዋነኛነት አማርኛ መናገርን ያስቀደመ ነው፡፡ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የመንግሥት ሃይማኖትና አንጋሽ ነበረች፡፡ ንጉሦችን የምትቀባ፣ በጦርነትም ታቦት ይዛ የምትዘምት እንደነበረች ይታወቃል፡፡ የአቢሲኒያ ኢምፓየር ሥሪቱ ይህ ሲሆን በባህሪው ተስፋፊ፣ ጠቅላይና ቅኝ ገዥያዊ ሥርዓት ነው፡፡ የአፍሪካ ቀንድን የአውሮፓ ኮሎኒያሊስቶች ሲቀራመቱት እርሱም የራሱን ድርሻ ቆርሶ በመውሰድ የተፈጠረ ነው፡፡ ምኒልክ ያደረጉት ልክ ፈረንሣዮች፣ እንግሊዞችና ጣሊያኖች በአካባቢው ሲያደርጉት እንደነበረው ነው፡፡

የኃይለ ሥላሴ መንግሥት በብሔር ብሔረሰቦች ትግል በዋናነት ሲገረሰስ አገሪቱ ሥሪቷ ሳይፈርስ በአንድነት መቀጠል ነው የሚያስፈልጋት ያሉ ሶሻሊስታዊ ኃይሎች አገር መምራት ጀመሩ፡፡ ፊውዳላዊው ሥርዓት ከተገረሰሰ ጭቆና በአገሪቱ አይኖርምና ሁሉም ማኅበረሰብ እኩል የሆነበት ኢትዮጵያን መፍጠር እንችላለን በሚል ሶሻሊስታዊ ርዕይ ነበር አገሪቱን የመሩት፡፡ እኛ ይህ የኦሮሞን ጥያቄ የማይመልስ ነው ብለን ተቃውመን ስንታገለው ቆይተናል፡፡ ኦነግ ለመጀመሪያ ጊዜ የኦሮሞ ሕዝብ ቋንቋው፣ ባህሉና ማንነቱ የተከበረበት የራሱ አገር ይኑረው ብሎ ፍላጎቱን ግልጽ አድርጓል፣ ለዚህም ሲታገል ነው የኖረው፡፡

ሪፖርተር፡- ኦሮሞ በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ውስጥ የራሱን ማንነት፣ ባህልም ሆነ ቋንቋ ማሳደግ ይችላል የሚሉ በርካቶች አሉ፡፡ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በፈጠራት ኢትዮጵያ ፍላጎቱን አስከብሮ መኖር ይችላል ብለው የሚያምኑ የፖለቲካ ኃይሎች አሉ፡፡   

አቶ በቴ፡- ብዙ ጊዜ ኦሮሞ ያልሆኑ ወገኖች መለየት ያቃታቸው ጉዳይ እሱን ነው፡፡ አንዳንዴ ጉዳዩን ኦነጋዊያን ብለው የሚመድቡት አሉ፡፡ የኦሮሞ ጥያቄ ምንድነው ብለው የሚያነሱት አሉ፡፡ ይህ ግን ሊገባቸው ስለማይፈልጉ ወይም እያወቁ ስለሚያድበሰብሱ የሚነሳ ጥያቄ ነው፡፡ ኦሮሞ ትልቅ ማኅበረሰብ ነው፡፡ በኦሮሞ ውስጥ ብዙ አመለካከቶች ቢኖሩ የሚደንቅ አይደለም፡፡ ቅኝ ገዥው ሥርዓት እስካሁንም የዘለቀ በመሆኑ የነበረው ጭቆና፣ የባህል ጫናና የማንነት ማሳነስ ብዙ ሰዎችን የተለያየ አመለካከት እንዲይዙ የሚያደርግ ነው፡፡ እኛ የምናነሳውን የኦሮሞ ጥያቄ የሚቃወሙ ኦሮሞዎች የሉም ብለን አናምንም፡፡ በኦሮሞ ውስጥ ሦስት ዓይነት የፖለቲካ ዝንባሌዎች አሉ፡፡ አንዱ ነባሩን አሀዳዊ ሥርዓት ማስቀጠል የሚፈልግ ነው፡፡ በምኒሊክም ሆነ በኃይለ ሥላሴ ዘመን ሥርዓቱን ያገለገሉ ነበሩ፡፡ በሥርዓቱ ውስጥ ቁንጮ የነበሩና ኃይለ ሥላሴም ጭምር በደም ኦሮሞ የሆኑ በርካታ ናቸው፡፡ በደርግም ቢሆን ኢትዮጵያ ወይም ሞት ብለው በኤርትራና ትግራይ ተራሮች የተሰውና ይህችን ኢምፓየር ለማስቀጠል ብዙ ዋጋ የከፈሉ የኦሮሞ ልጆች ነበሩ፡፡

በሌላ በኩል ፌዴራላዊት ኢትዮጵያን እንደግፋለን የሚሉ ኃይሎችም አሉ፡፡ በኢትዮጵያ ግንባታ ሁሉንም ዓይነት ሚና ነበረን፣ በታሪክ አጋጣሚ ተዋህደናል ተዋልደናል፣ ብዙ አገሮችም የሚፈጠሩት በዚህ መንገድ ነው የሚሉት እነዚህ ኃይሎች የራሳችንን ዕድል በራሳችን የመወሰን መብት ሳንነጠቅ በፌዴራላዊ ሥርዓት ከሌሎች ሕዝቦች ጋር መኖር ይሻላል የሚሉ ናቸው፡፡ በራሳችን ክልል ራሳችንን እያስተዳደርን ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር በሰላምና በጋራ መኖር ለኦሮሞ ሕዝብ ይበቃዋል የሚሉ ናቸው፡፡ የራስን ዕድል በራስ መወሰን ከኢትዮጵያ ማዕቀፍ መውጣት ሳይሆን፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ከመገንጠል ውጪ ራስን በራስ እያስተዳደሩ መኖር ነው  የሚሉ አሉ፡፡ እኛ የነፃነት ኃይሎች ግን በታሪክ አጋጣሚ በእንዲህ ዓይነት የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ብንጠቃለልም ወደ ነበረን የቀደመ የብሔር ክብር መመለስ እንችላለን ብለን እናምናለን፣ አለብንም፡፡ ነፃ አገር ለመሆን የሚያግደን ነገር የለም፡፡ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በሚሊታሪም ሆነ በጂኦግራፊ ትልቅ ሕዝብ ስለሆንን ራሳችልን ችለን መቆም እንችላለን፡፡ ነገር ግን የኦሮሞ ሕዝብ ፍላጎቱ ከሆነ ከሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር የመኖር መብቱ ሊከበር ይገባል፡፡ ይህ በቂው ነው ብለን መወሰን ግን ተገቢ ነው ብለን አናምንም፡፡

የኦሮሞ ሕዝብ እስከ ዛሬም የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን ዕድል አላገኘም፡፡ ይህ ዕድል ተሰጥቶት በፈቃዱ ከመረጠና በኢትዮጵያ ውስጥ መኖር እፈልጋለሁ ካለ መብቱ ነው፡፡ አልያም እኛ እንደምንለው ነፃ መንግሥት እፈልጋለሁ ካለ አገር የመመሥረት መብቱ ሊከበርለት ይገባል እንላለን፡፡ እኛ ይበቃዋል ብለን የምንገድበው አይደለም፡፡ አንደኛ ኦሮሞ ብሔር ነው፣ ብሔር ደግሞ አገር መሆን ይችላል፡፡ ሁለተኛም ኦሮሞ በግድ ነው የተጠቃለለው፡፡ በግድ ሥርዓት የተጫነበት ሕዝብ ደግሞ ራሱን መግለጥ መቻል አለበት፡፡ ድርጅታችን ወደ አገር ቤት ሲመለስም በሕጋዊ መንገድ ኦሮሞ አገር የመሆን መብቱን መጎናፀፍ ይችላል ብሎ በማመን ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 39 በግልጽ እንደተቀመጠው ኦሮሞ ለዘመናት የታገለለትን ያን መብቱን በሕግ ማዕቀፍ ማግኘት ይችላል ብለን ነው የምንታገለው፡፡ ኢሕአዴግ በሕግ ቢያስቀምጥም በአሠራር ግን ያስቀመጠውን የሚቃረን አሀዳዊ በመሆኑ ያንን ዓይነት የውሸት ፌዴራላዊ ሥርዓት ተቃውመናል፡፡

ሪፖርተር፡- ደርግ በወደቀ ማግሥት በነበረው የሽግግር ሒደት ስድስት የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ተሳትፈዋል፡፡ ኦነግ በወቅቱ ከሕወሓትም ሆነ ከሻዕቢያ ያልተናነሰ የመሣሪያም የፖለቲካም አቅም ነበረው፡፡ አሁን ያለው ሕገ መንግሥት እኮ የሕወሓትና የኦነግ የፖለቲካ ዶሴ ነው ተብሎ ይተቻል፡፡ ሕገ መንግሥቱንም ሆነ ፌዴራላዊ ሥርዓቱ የሚቃወሙ ኃይሎች በሽግግሩ ሒደት አልተወከልንም ይላሉ፡፡ በዚያ ወቅት በብዙ የፖለቲካ ኃይሎች የተወከለው ኦሮሞ በፌዴራላዊ ሥርዓቱ ለመቀጠል አልመረጠም ሲባል ከዚህ ጋር አይጋጭም ወይ? ሥርዓቱ የተገነባበትን ነባራዊ ሀቅ መካድ አይደለም ወይ?

አቶ በቴ፡- በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው የተነሳው፣ ሆኖም ታሪክን መካድ አይደለም፡፡ ለዚህ መልስ የታሪክ ነጠብጣቦችን በትክክል ማገናኘት አስፈላጊ ነው፡፡ የሽግግሩ ቻርተር የኦነግ አመራሮች በግልጽ የተሳተፉበት ነው፡፡ ሰናፌ ላይ ቅርፁን የያዘው የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር ሌንጮ ለታ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉት ቻርተር ነው፡፡ በዚያም ከለንደን ኮንፈረንስ በኋላ በነበረው ሻዕቢያና ሕወሓት ያልካቸው ኃይሎች የነበሩበት ስምምነት ውስጥም ኦነግ ነበረበት፡፡ የኃይል መመጣጠን ነበር የሚባለው ግን የተጋነነ ነው፡፡ የፖለቲካና የኃይል አሠላለፍ በአብዛኛው ለብዙዎች ይምታታል፡፡ በፖለቲካ ኃይል ከሆነ ኦነግ በጊዜው ከሕወሓትም በላይ ገዝፎ ነበር፡፡ በሌሎች ማኅበረሰቦች ጭምር ትልቅ ተቀባይነት አግኝቶ ነበር፡፡ አቶ ገላሳ ዴልቦ ጎንደር ሄደው ያደረጉት ንግግር ታሪካዊ ነው፡፡ ወልዲያ ላይ ኦነግ ቢሮ ከፍቶ ነበር፡፡ አዲስ አበባም ሆነ ሌሎች አካባቢዎች ሰፊ የማኅበረሰቡን ድጋፍ አግኝቶ ነበር፡፡ ከምርጫ በፊት በነበረው ቅድመ ምርጫ (ስናፕ ኢሌክሽን) ኦነግ በአዲስ አበባ 70 በመቶ አሸንፎ ነበር፡፡

ይህ ሁሉ የፖለቲካ የበላይነት የነበረው ኦነግ ግን በጊዜው ከሕወሓት ወይ ከሻዕቢያ የሚሊታሪ የበላይነት ነበረው ማለት አይቻልም፡፡ ሕወሓት፣ ብአዴን፣ ኦሕዴድና ደኢሕዴግ ተብሎ በመቀላቀል ኢሕአዴግ በአደረጃጀት የፈጠረው ኃይል ቀላል አልነበረም፡፡ ወደ ሽግግሩ ሲገባ ሕወሓት 150 ሺሕ፣ እንዲሁም ሻዕቢያ 200 ሺሕ ሠራዊት የነበራቸው ሲሆን ኦነግ ግን 20 ሺሕ ጦር ነው የነበረው፡፡ በፖለቲካው ኦነግ ተቀባይነትና የበላይነት ቢኖረውም ነገር ግን በሚሊታሪው አለመመጣጠን ነበር፡፡ ከቅድመ ምርጫው (ስናፕ ኢሌክሽን) በኋላ ግን በኢሕአዴጎች ዘንድ ከፍተኛ መደናገጥ በመፈጠሩ ከፍተኛ ርብርብ በኦነግ ላይ ተጀመረ፡፡ በብዙ የኦሮሚያ አካባቢዎች የሕወሓትና የኢሕአዴግ ጦር ሰፍሮ ነበር፡፡ የኦነግን መዋቅርና ካድሬ ማደን ተጀመረ፡፡ ኦነግ የነበረው በቻርተሩ ጊዜ ነበር፡፡ ሕገ መንግሥቱ ረቆ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት እስኪጀመር ማለትም ከ1984-87 ዓ.ም. ባለው ጊዜ የሽግግር መንግሥቱን የሚመራ መንግሥት ለመመሥረት ምርጫ ይደረግ ሲባል፣ ኦነግ የሁላችንም ታጣቂ መሣሪያውን አስቀምጦ ለተሃድሶ ወደ ወታደራዊ ካምፕ ይግባ የሚል ጥያቄ አቀረበ፡፡ ይህን ደግሞ ኢሕአዴግም ሻዕቢያም ደገፉ፡፡ የሦስትዮሽ ኮሚቴ በአሜሪካ መንግሥት ተዋቅሮ ሠራዊታቸው ወደ ካምፕ እንዲገቡ ተደረገ፡፡ ኦነግ የፖለቲካ የበላይነት ስለነበረውና በምርጫ እንደሚያሸንፍም በመተማመን ነበር ሙሉ ሠራዊቱን ወደ ካምፕ ያስገባው፡፡ ይሁን እንጂ ኢሕአዴግ ወደ ካምፕ የተወሰነውን ልኮ በቀረው ኃይል የኦነግን ሠራዊት ማሳደድ ጀመረ፡፡ ማምለጥ የቻሉት የኦነግ አመራሮች ወደ ጫካ ገቡ፡፡ ኦነግም በዚያ መልክ ከቻርተሩ ተገፍቶ ወጣ፡፡ ምርጫ ላይ አልደረሰም፣ ሳይሳተፍ ነው የተገፋው፡፡ በቻርተሩ ጊዜ ግን ኦነግ 12 ወንበሮች ነበሩት፡፡ እንዲያውም በአንዳንድ አጋጣሚዎች የደቡብና የሌሎች አካባቢ ተወካዮችን ከጎኑ በማሠለፍ የድምፅ የበላይነት ሁሉ ያስመዘግብ ነበር፡፡ ኦነግ 52 የቻርተሩ ተወካዮችን ድምፅ በማስመዝገብ ኢሕአዴግን አሸንፎ ያስወሰነበት ጊዜ ሁሉ ነበር፡፡ ይህ የፖለቲካ ቅቡልነቱ ነው ለኦነግ ጠላት የፈጠረለት፡፡ ኦነግ የተገፋው ደግሞ በሰኔ የሽግግር መንግሥት ምርጫ ሊካሄድ ቀጠሮ በተያዘበት ሰሞን ነበር፡፡

በወቅቱ የተስማሙት የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት በሕገ መንግሥቱ መፍትሔ ስለሚበጅለት፣ በሒደት የኦሮሞ ሕዝብም መወሰን ይችላል በሚል ነበር፡፡ ኦነግ በወቅቱ ሻዕቢያ አሸንፌያለሁና የኤርትራን መንግሥት መሥርቻለሁ በሚል የሄደበትን መንገድም ተቃውሞ ነበር፡፡ ይህን ያደረገው ደግሞ የሽግግር ሒደቱ ታልፎ በሕጋዊ መንገድ ውሳኔው ይደረስበታል ከሚል ቀና የፖለቲካ አመለካከት ነበር፡፡ የፖለቲካ ተንኮልን ሳያገናዝብ የኦነግ አመራር በወሰደው ውሳኔ ዋጋ እንዲከፍል ተደረገ፡፡ በሕዝቦች እኩልነት መንፈስ የፌዴራል ሥርዓቱ ቢመሠረት እዚያ ላይ የከረረ ጥላቻ የለንም፡፡ ለዚያ ነበር ኦነግ የተለሳለሰው እንጂ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጉዳይን ኦነግ ከፕሮግራሙ አላነሳም፡፡ በሽግግር ሒደቱ የተወሰኑ የፖለቲካ ኃይሎች አልተሳተፉም ሲባል እሰማለሁ፡፡ በተለይ የአማራ ድርጅቶች አልነበሩም፣ አማራ አልተወከለም ሲባል እሰማለሁ፡፡ በወቅቱ ግን የአማራ ድርጅቶች አልነበሩም፡፡ የተገፉት እንዲያውም የኢትዮጵያ አንድነትን የሚያቀነቅኑት የመኢሶንና የኢሕአፓ ድርጅቶች ነበሩ፡፡ ብአዴን የአማራ ድርጅት አይደለም የሚለውን ክርክር ወደ ጎን ብዬ ከብአዴን ውጪ የአማራ ድርጅት አልነበረም፡፡ የአማራ ልሂቃን የሚባሉት እነ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ይከራከሩ የነበረው ግን አማራ የሚባል የዘውግ ማንነት የለም ብለው ነበር፡፡ አማራ የሚባል የዘውግ ማለትም በደም የሚተላለፈው የዘር ወይም የብሔር ማንነት የለም ብለው ሲከራከሩ፣ እንዲያውም እነ መለስ ዜናዊ ነበሩ አለ ብለው የተቃወሙት፡፡ አማራ የሚባል የጋራ ቋንቋ፣ ባህልና ሥነ ልቦና ያለው ማኅበረሰብ እስካለ ድረስ አማራ ሊወከል ይገባል ያሉት ኢሕአዴጎች ናቸው፡፡ ያን ግን ፕሮፌሰሩና በጊዜው የነበሩ የአማራ መሪ ልሂቃኑ ከሰውነት ማነስ አድርገው ነበር የቆጠሩት፡፡ ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ ዩኒቨርሲቲውን ወክለው ነበር በወቅቱ የተካፈሉት እንጂ አማራን አላሉም፡፡ እርሳቸው ንቅናቄ ነበር የመሠረቱት፡፡ ንቅናቄው ግን የፖለቲካ ጥያቄዎች ያነሳ ስለነበር ሲቪክ ማኅበር ሆናችሁ ማንሳት አትችሉም ስለተባሉ ነበር መአሕድ (የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት) ወደ መመሥረት የገቡት፡፡ አብዛኛው የአማራ ምሁር እኛ ከኢትዮጵያዊነት ወርደን በአማራነት አንደራጅም ነበር ያለው፡፡  

ሪፖርተር፡- የአማራ ኃይሎች ብቻ አይደለም እኮ በወቅቱ ሥርዓቱ ሲፈጠር አልተካፈልንም የሚል ጥያቄ የሚያነሱት፡፡ በብሔር ማንነት አንደራጅም ያሉ ኢትዮጵያዊ ነን የሚሉ ወገኖችም ሥርዓቱ ሲፈጠር አልተወከልንም ይላሉ እኮ?

አቶ በቴ፡- እርሱን በግሌ በደንብ እቀበላለሁ፡፡ የታገዱት መኢሶንም ሆነ ኢሕአፓ ኢትዮጵያዊ ኃይሎች ናቸው፡፡ በኢሕአዴግ ውስጥ የነበረው ብአዴን ግን በአማራ ክልል ከቀበሌ ጀምሮ ሕዝቡን ሲያደራጅ ነበር፡፡ አማራን እወክላለሁ ብሎ ክልሉን ሲመራ  ነበር፡፡ ሕገ መንግሥቱም ቢሆን በአማርኛ ነው የተጻፈው፡፡ ይህ ሁሉ ታልፎ አማራ አልተወከለም ማለት ለእኔ አይዋጥልኝም፡፡ በሽግግሩ ውስጥ የነበሩ ኦሮሞ ድርጅቶች ሁሉም ተገፍተው ወጥተው ኦሕዴድ ብቻ ነበር የቀረው፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ግን እኛ በሒደቱ አልተወከልንም አላልንም፡፡

ሪፖርተር፡- አማራ መወከል የምፈልገው በኢትዮጵያዊ ኃይሎች ነው ብሎ ከሆነስ? የኢትዮጵያ ኃይሎች መገፋታቸውን ደግሞ ተቀብለውታልና ከዚህ አንፃር አልተወከልኩም የሚለው ከመጣስ?

አቶ በቴ፡- አማራ በኢትዮጵያዊ ኃይሎች ነው መወከል የምፈልገው ብሎ የወጣበትን ጊዜ አይቼ አላውቅም፡፡ እንዲያውም በተቃራኒው ነው ሲሆን የማየው፡፡ ለምንድነው እነ ኢዜማ ከባህር ዳር የተባረሩት?

ሪፖርተር፡- አሁን ያለው የፖለቲካ ስሜት ከ1983 ዓ.ም. ፍፁም የተለየ መሆኑ ይታወቃል እኮ፡፡

አቶ በቴ፡- አዎን የተቀየረ ነው፡፡ ነገር ግን ያን ጊዜም ቢሆን ‹‹ፖፑላር ሰፖርት›› (ሕዝባዊ ድጋፍ) እንጂ፣ በተጨባጭ በኢትዮጵያውያን ኃይሎች ልወክል ብሎ የተሰባሰበ ወገን አልነበረም፡፡ ውክልና መደበኛ በሆነ መንገድ የሚወከለው ወገንን ፈቃድ ማግኘት ይጠይቃል፡፡ የተወካይ ውክልናን በሕጋዊ መንገድ መቀበል ይጠይቃል፡፡ እንዲሁም የምትወክለው ነባራዊ ሀቅ ሊኖር ይገባል፡፡ በፌስቡክ እንደሚታየው አልተወከለም የሚል ዘመቻ ማድረግ ሳይሆን በመደበኛ መንገድ ተደራጅቶ፣ ተፎካክሮ፣ አሳምኖ ውክልናን መያዝ ይጠይቃል፡፡ እውነት ለመናገር አሀዳዊው ኃይል ግን በወቅቱ የተሸነፈ ኃይል ነበር፡፡ ጦርነት ነበር፡፡ ኢትዮጵያዊ ነን የሚሉ ኃይሎችም ተሸንፈው ነበር፡፡ መኢሶንም ሆነ ኢሕአፓ እኮ በጊዜው ከደርግ የተለዩ አልነበሩም፣ ሁሉም አሀዳዊያን ነበሩ፡፡ ኦነግ፣ ሕወሓትና ሻዕቢያን ጨምሮ ለብሔር የታገሉ ናቸው፡፡ ሥልጣን እንጂ አይዲዮሎጂ (ርዕዮተ ዓለም) አይለያያቸውም፡፡ አሸንፎ የመጣው የራሱ ራዕይ ነበረው፡፡ በብሔር መደራጀት ላይ የተመሠረተ ፖለቲካን ይፈልግ ነበር፡፡ ብሔሮች እንዳይጨቆኑ ዋስትና የሚሰጥ የፖለቲካ ሥርዓት ይፈልግ ነበር፡፡ ይህም ቢሆን ግን የተሸነፈውና ተገፋ የተባለው ኢትዮጵያዊ ኃይል እንዲገፋ ኦነግ አይፈልግም ነበር፡፡ መገፋታቸውን ተቃውሟል፡፡ በጊዜው የሕዝብ ድምፅ ይብዛም ይነስም መወከል አለበት ብለን ተቃውመናል፡፡ ደርግም ቢሆን በሽግግሩ ቢካተት ኦነግ ቅሬታ አልነበረውም፡፡

ሪፖርተር፡- ባለፉት 30 ዓመታት የመገፋፋት ፖለቲካ አልነበረም ወይ የነገሠው? አገሪቱ በመሠረታዊ የአገር መገለጫዎች እንኳ መስማማት ያቃታት በዚህ የተነሳ አይደለም ወይ? በአንድ ባንዲራ፣ በአንድ ብሔራዊ መዝሙርና በሌሎችም የአገር መገለጫ እሴቶች መስማማት የጠፋው በዚህ የመገፋፋት ፖለቲካ አልነበረም ወይ?

አቶ በቴ፡- የኢሕአዴግም ችግር ሥልጣንን በኃይል አግኝቻለሁና በኃይል አስጠብቃለሁ ብሎ ማመኑ ነው፡፡ ደርግን ደምስሻለሁና በኃይል ፍላጎቴን ላስፈጽም የሚል አካሄድ ነው በእኛና በኢሕአዴግ መካከል ፀብ የፈጠረው፡፡ ለመታገል ከእኛ የቀደመ ባይኖርም አራት የሚኒስትርነት ቦታ ጥለን ነው የወጣነው፡፡ የኢሕአዴግን ጠቅላይነት ስንቃወም ነው የኖርነው፡፡ በዚህ እኛ ልንወቀስ አንችልም፡፡ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለው ኃይል ቢሆን የሌላውን የፖለቲካ ኃይል አመጣጥ መረዳት መቻል አለበት፡፡ በጊዜው የተገፋው ኢትዮጵያዊ የሚባለው ኃይል አልነበረም፡፡ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለው ኃይል እንዲያውም የተደራጀና በተገቢው የሚመራ ኃይል አልነበረም፡፡ አሁን ሊኖር ይችላል፣ በዚያን ጊዜ ግን ከወደቀው ኢሠፓ በቀር አንድም ኃይል አልነበረም፡፡ ሀቀኛ የፖለቲካ ትግል ያደረጉ ድርጅቶችም ተገፍተው ወጥተዋል፡፡ ኦነግ፣ የሲዳማ አርነት ንቅናቄ፣ ኦብነግ፣ በጃራ አባገዳ የሚመራው፣ የዋቆ ጉቱ ኃይል ተገፍተዋል፡፡ ስለዚህ ኢሕአዴግ በወጣውም ሕገ መንግሥት የሚያምን አልነበረም፡፡ ኢሕአዴግ የፈጠረው ሥርዓት ፌዴራላዊ ይባል እንጂ በገቢር አሀዳዊ ነበር፡፡ ሥርዓቱ ለፌዴራላዊ ኃይሎች ያደላና ኢትዮጵያዊ ኃይሎችን ብቻ የሚገፋ አልነበረም፡፡ ኢትዮጵያዊ የሚባለው ኃይልም ቢሆን ከጥቂት የሚዲያ ጩኸት በዘለለ ብዙዎች የሚደግፉትና የሚሞቱለት የፖለቲካ አሠላለፍ አይመስለኝም፡፡ ትንሽ ሲገለጥ አማራዊ ኃይል ሆኖ ነው የሚገኘው፡፡ መአሕድ የተባለው አማራ ድርጅት በሒደት መኢአድ ተብሎ ነው መታገል የጀመረው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔርተኝነት ተብሎ በራሱ የቆመ ሁሉንም አካታች የሆነ የፖለቲካ ዕሳቤ የለም፡፡ አማራና የቀደመው የዘውዳዊ ሥርዓት የሚንፀባረቁበት ነው የሚታየው፡፡ ኢትዮጵያን ወደ ቀደመ ማንነቷና ገናናነቷ እንመልሳለን የሚል ቁመና ነው የሚታየው፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያን የሠራው ሁሉም ብሔር አይደለም? ከአፄ ምኒልክ ዘመንም አልፈን ብንሄድ ኦሮሞ በጎንደር ቤተ መንግሥት የነገሠበትን ታሪክ፣ የሀዲያ ንግሥት ማዕከላዊ መንግሥቱን የመራችበት፣ የዛጉዌ ሥርወ መንግሥት የተመሠረተበትንና ሌላም ታሪክ አናገኝም ወይ? ኢትዮጵያ ሁሉም ሕዝብ አሻራውን ያሳረፈባት አገር አይደለችም እንዴ?

አቶ በቴ፡- አይደለም፡፡ በአገልጋይነት የገባውን መቁጠር የአንድን ማኅበረሰብ የፖለቲካ ተሳትፎ አያሳይም፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ከመጣው የእንግሊዝ ጦር አብዛኛው ህንዳዊ ወታደር ነበር፡፡ ነገርዬው ህንድ ኢትዮጵያን ወረረች አያሰኝም፡፡ የእንግሊዝ ኢምፓየር የህንድ ነበር አያስብልም፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያን ሁኔታ በቅኝ ግዛት መሥፈርት ማስቀመጥ እንዴት ይቻላል?

አቶ በቴ፡- ቅኝ አገዛዝ ነው የምንለው፡፡ የሩሲያ ዓይነት ታሪክ ነው እኮ የእኛም፡፡ የሶቪዬት ኅብረት ቁንጮ የሆነው ስታሊን ጆርጂያዊ ነበር እኮ፡፡ ሶቪዬት ስትፈራርስ ጆርጂያ ነፃ አገር ሆናለች፡፡ ስታሊን ሶቪዬትን ስለመራ ሩሲያ ሆነን መቀጠል አለብን አላሉም፡፡ ኃይለ ሥላሴ በአባት ኦሮሞ ናቸው፡፡ ነገር ግን ንግሥና ስለፈለጉ የእናት ሐረግን ቆጥረው ዘውዱ ይገባኛል ብለዋል፡፡ አማራዊ ሥነ ልቦናን፣ ኦርቶዶክሳዊ እምነትንና አቢሲኒያዊ ሥርዓትን ተቀብለው ነው የኖሩት እንጂ የኦሮሞን ገዳ አልተቀበሉም፡፡ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ ልጅ ኢያሱ ከሚነግሥ እርስዎ አገር ይምሩ ተብለው ቢጠየቁም፣ እኔ የንጉሥ ዘር አይደለሁም ብለው ውድቅ አድርገዋል፡፡ ይህ የአቢሲኒያዊ ፖለቲካ ተፅዕኖ ነው፡፡ መጽሐፉ ፍትሐ ነገሥትም ቢሆን የሚተርከው ይህንኑ ነው፡፡ ይህን ስንቃወም ነበር፡፡ ከደርግ ውድቀት በኋላም ቢሆን የነበረውን ሥርዓት ኅብረ ብሔራዊ ለማድረግና እሱንም ላለማጣት ነው ኦነግ ሲታገል የኖረው፡፡ ኢሕአዴግን ሕወሓታዊ ሥርዓት ነው ሲባል የነበረው እኮ እነ ኦሕዴድ ቢኖሩም ሁሉንም አድራጊና ፈጣሪው ሕወሓት ስለነበር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እናንተ ጫካ ገብተናል፣ መስዋዕትነት ከፍለናል ብትሉም እንወክለዋለን ለምትሉት ለኦሮሞ ሕዝብ ከኦሕዴድ የተሻለ ምን አስገኝታችኋል? የኢሕአዴግ ተለጣፊ ስትሉት የቆየው ኦሕዴድ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄዎች እንዲመለሱ ታግሎ ብዙ ድል አስገኝቷል የሚል ክርክር ይነሳል፡፡

አቶ በቴ፡- ትክክል አይደለም፡፡ ለኦሮሞ ብዙ አሳክተናል፡፡ ከኦሕዴድ የተሻለ የሚያደርገን ብዙ ነገርም አለ፡፡ የኦሮሞን ባህል ዳግም እንዲመለስ በማድረግ በኩል ኦነግ ብዙ ሠርቷል፡፡ የኦሮሞን ቋንቋን በማስተማርና በሌሎችም ሥራዎች ኦነግ ከሽግግሩ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ በአንድ ዓመት ጊዜ ብዙ ምሥጉን ሥራዎች ሠርቷል፡፡ ኦሕዴዶችን ጭምር ኦነግ ነበር ቁቤ ያስተማረው፡፡ ኦነግ ወሎ የኦሮሞ ነው ብሎ ተከራክሮ ነበር፡፡ አሁን ያለው የኦሮሚያ ካርታ የተሠራውም በኦነግ ትግል ነው፡፡ ኦነግ የታገለባቸው ብዙ ጥያቄዎች ኦነግ ከተገፋ በኋላ ተጨናግፈዋል፡፡ ለምሳሌ ወሎ ወደ ኦሮሞ የመመለሱ ጥያቄ ተጨናግፏል፡፡ ጅግጅጋ የኦሮሚያ ክልል የነበረች ሲሆን፣ ሶማሌ በተውሶ ወስዶ ነው ዋና ክልሉ ከተማ የሆነችው፡፡ ድሬዳዋንም እስከ መካፈል የደረሰው፡፡ አዲስ አበባ የፌዴራል ይሁን ተብላ በማይታወቅ መዋቅር ውስጥ እንድትወድቅ ተደረገ፡፡ ይህ ሁሉ የጨነገፈው በኦሕዴድ ችግር ነው፡፡ ኦሕዴድ አሳካው የሚባለው ነገር ካለ ማሳካት የቻለው በኦነግ ትግል ነው፡፡ የኦነግ ትግል ባይኖር ኦሕዴድ በጠራራ ፀሐይ ተባራሪ ድርጅት ነበር፡፡ በታሪክ አጋጣሚ ለማ መገርሳ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት በግል ስናወራ፣ ኦነግ ስላለ ነው እኛ ክብር ያገኘነው ብለው ነግረውኝ ያውቃሉ፡፡ ኦሕዴዶች ክብር ያገኙት በኦነግ ተጋድሎ ነው፡፡ ኦነግ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ተውሰው ነው በኢሕአዴግ ውስጥ የታገሉት፡፡ ላም ወልዳ ጥጃ ሲሞትባት ወተት መስጠት እንዳታቆም በሚል፣ የሞተችው ጥጃ ቆዳ በጭድ ይሞላና በሕይወት ያለች እንድትመስል አድርጎ ላሟ እንድትልሳት ይደረጋል፡፡ ይህን ስታደርግም ወተት ትሰጣለች፡፡ በኢሕአዴግ ወቅት እነርሱ እዚህ ግባ የሚባል የፖለቲካ ሰብዕና አልነበራቸውም፡፡ በራሳቸውም አንደበት ተላላኪ ነበርን ብለው ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ የኦነግን ትግል የሚያሳንሱ አሉ፡፡ ነገር ግን ለምን አፈናውን አቁመው ኦነግ በነፃ ምርጫ እንዲሳተፍ አያደርጉንም፡፡ በሕጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሰውን ኦነግ ቢሮውን አፍኖ ማቆየት ለምን አስፈለገ?

ሪፖርተር፡- እናንተ በሰላም ለመንቀሳቀስ ዝግጁ ናችሁ?

አቶ በቴ፡- ለዚያ አይደለም እንዴ ወደ አገር ቤት የገባነው? ስምምነትም የተደረገው?

ሪፖርተር፡- ከገባችሁ በኋላ የነበረው ሁኔታ በተለይ ከትጥቅ መፍታት፣ እንዲሁም በሰላም ከመንቀሳቀስ ጋር በተገናኘ ያራመዳችሁት አቋም የምትሉትን የሚደግፍ ነበር ወይ?

አቶ በቴ፡- የኢትዮጵያ ሚዲያ አንድ ወገን ስለሚከተል እንጂ፣ እኛ ወደ አገር ቤት ከገባን በኋላ ስምምነታችንን ያከበረ አቋም ነው ያራመድነው፡፡ ይህን ደግሞ በተደጋጋሚ ገልጸናል፡፡ የኦነግ ሠራዊት ትጥቅ ይፈታል፡፡ ኦነግ ከሽብር መዝገብ ተፍቆ በሰላም ይንቀሳቀሳል፡፡ በይቅርታ አዋጅ መሠረት ከዚያ ቀደም ለተፈጸሙ ወንጀሎች ማንም የኦነግ አባልና አመራር በወንጀል አይጠየቅም፡፡ ጦሩ ደግሞ ትጥቅ ፈትቶ ወደ ካምፕ ገብቶ ተሃድሶ ተሰጥቶት ወደ ፀጥታ መዋቅር ወይም ወደ ሌሎች ሥራዎች እንዲሰማራ ዕድል ይመቻችለታል፡፡ የተወሰዱ የኦነግ ድርጅቶች ኦራ የሚባል ኢንዶውመንት ድርጅትን ጨምሮ የተዘረፉ ብዙ ንብረቶቹ ይመለሱለታል፡፡ በጦርነቱ የት እንደደረሱ ያልታወቁ አባሎች በጋራ ኮሚቴ ማፈላለግ ይደረጋል የሚሉ ነበሩ ስምምነቶቹ፡፡ ከተገባ በኋላ ግን ስምምነቱን በአግባቡ ተፈጻሚ ሳያደርጉ ቆዩ፡፡ በዚህ የተነሳ ነው አሁን ጫካ ያሉት ኃይሎች ወደ እዚህ ሁኔታ የገቡት፡፡ መጀመሪያ ኦነግ ቅቡልነት የለውም ብለው አስበው ነበር፡፡ አገር ቤት ሲገባ ግን የገጠመው የሕዝብ ድጋፍ አስፈራቸው፡፡ ለዚህ ነው ጫና የሚያደርጉብን፡፡

ሪፖርተር፡- ፓርቲያችሁ በምን ሁኔታ ላይ ነው የሚገኘው?

አቶ በቴ፡- ቢሯችን ታሽጎ ነው ያለው፡፡ አመራሮቻችን ታስረው ነው የሚገኙት፡፡ በምርጫ ቦርድ ሕጋዊ ብንሆንም በብልፅግና ግን ሕገወጥ ተብለን ነው የምንገኘው፡፡ መንግሥት ደቡብ አፍሪካ ድረስ ከታጠቀ ኃይል ጋር የሰላም ስምምነት ለመፈራረም ሲሄድ ዓይተናል፡፡ በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ በምንቀሳቀሰው በእኛ ላይ ለምን ይህን ሁሉ አፈና ያደርስብናል? ከታጠቁ ኃይሎች ጋር የጀመሩትን ሰላም ማስፈን ጥረት ገፍተው ከቀሩት የታጠቁ ኃይሎች ጋር በሰላም ለመፍታት መጣር አለባቸው፡፡

ሪፖርተር፡- በኦሮሚያ ክልል ንፁኃን በተደጋጋሚ ይገደላሉ፡፡ በንፁኃን ግድያ፣ በደሃ ገበሬዎችና ከፖለቲካ ጋር ምንም ግንኙነት በሌላቸው ዜጎች እልቂት የሚመለስ የኦሮሞ የፖለቲካ ጥያቄ አለ ወይ? እናንተ ለምን ይህን ዓይነት ዘር ተኮር ገጽታ ያለው ጭፍጨፋ አታወግዙም?

አቶ በቴ፡- የምናወግዘው ሁለቱንም ነው፡፡ መንግሥትንም ሆነ ሌላውን እናወግዛለን፡፡ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርስ ጭፍጨፋን በማንም ይፈጸም እናወግዛለን፡፡

ሪፖርተር፡- ከሽግግሩ ጊዜ ጀምሮ በሐረርጌና በሌሎች አካባቢዎች ጭፍጨፋው ነበረ፡፡ ሆኖም ተጠያቂነት አይታይም፡፡ በበደኖና በሌሎች ቦታዎች ጥቃት ነበር፡፡ አሁን ደግሞ በወለጋ በስፋት እየታየ ነው፡፡

አቶ በቴ፡- ኦነግ በታሪኩ ሕዝብን የጥቃት ዒላማው አድርጎ አያውቅም፡፡ ማንንም ብሔር የጥቃት ዒላማ የማያደርግ ድርጅት ነው፡፡ ኦነግ ሥርዓትን ነው ሲታገል የኖረው፡፡ የኦሮሞ ጉዳትና ጭፍጨፋ ስለማይነገር እንጂ በሌሎች ማኅበረሰቦች ላይ ከደረሰው በላይ ነው እየደረሰበት ያለው፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ከሌላው ሕዝብ ጋር አብሮ የኖረ ነው፡፡ ይህን ማኅበረሰብ ከሌላው ሕዝብ ጋር ለማጋጨት የሚደረግ ጥረት ካልሆነ በስተቀር፣ የኦሮሞ ሕዝብ ሆደ ሰፊና ሁሉንም ተቀባይ ሕዝብ ነው፡፡ እልም ያለ አንፊሎ፣ በደሌና ኢሉአባቦር ጫካ ውስጥ አማራና ኦሮሞ አብረው ይኖራሉ፡፡ አብረው ያርሳሉ፣ አብረው ያመልካሉ፣ አብረው ቡና ይጠጣሉ፡፡ እንዲህ የተጣበቀውን ማኅበረሰብ ለምንድነው የምናባላው? እኛ ሥርዓት እንጂ ብሔረሰብ አይደለም የምንቃወመው፡፡ በኦሮሚያ ውስጥ ያሉ ከኦሮሞ ውጪ ያሉ ብሔረሰቦች የእኛው ዜጎች ናቸው፡፡ ኦነግ የበሰለ ፖለቲካ የሚያራምድ ድርጅት ነው፡፡ ኦሮሞ በተፈጥሮው ዘር ሳይቆጥር ሰዎችን አቅፎ የሚቀበል ሕዝብ ነው፡፡ በገዳ፣ በሞጋሳና በጉዲፈቻ ከኦሮሞ ሳይወለዱም ኦሮሞ ይኮናል፡፡

ሪፖርተር፡- ነፍጠኛ፣ መጤ፣ ሰፋሪና ሌሎች ፍረጃዎች ሌላውን ወገን አያስበረግጉም ወይ? አብሮ ለመኖርና ሌላውን ዋስትና እንዲሰማው የሚያስችሉ ናቸው ወይ?

አቶ በቴ፡- ኦነግ ሕዝብ ላይ ያተኮረ ትግል አድርጎ አያውቅም፡፡ አንዳንድ አዳዲስ ብሔርተኞች ኦሮሞን በመጥፎ ለመሳል የሚያቀርቡ አሉ፡፡ ኦነግ ከሚያራምደው የተሻሉ ብሔርተኛ አድርገው ራሳቸውን የከረረ ብሔርተኛ ሲያደርጉ ይታያሉ፡፡ አንዳንዶች ከኦነግ የተሻሉ ድርጅት መሆናቸውን ለማሳየት አንዳንዴ የኦነግን ቁንጽል ነገር ወስደው የከረረ ብሔርተኝነት ያራምዳሉ፡፡ ነገር ግን የእኛ ብሔርተኝነት የበሰለና ዴሞክራሲያዊ ነው፡፡ ሌላውን ማጥቃትን እንቃወማለን፡፡ ከኢሕአዴግ ዘመን ጀምሮ በኢትዮጵያ የተፈጠሩ ብሔር ተኮር ጥቃቶች ግን አብዛኞቹ በመንግሥት የፖለቲካ ሴራ የተቀነባበሩ ናቸው፡፡ እኛ ይህን እንቃወማለን፡፡ የሐረርጌውና አርባ ጉጉው እኮ በገለልተኛ መርማሪ እንዲጣራ እንፈልጋለን ብለን ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን ይህንን እያልን ነው፡፡    

 ሪፖርተር፡- የሰሜኑን ግጭት በሰላም ለመፍታት ተችሏል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ያለውን ቀውስ ለመፍታት ምን ቢደረግ ይሻላል?

አቶ በቴ፡-  በዚህ ላይ የእኛ አቋም ግልጽና ወጥ ነው፡፡ በአጠቃላይ ከአስመራ ስንገባም የኦሮሞ ሕዝብን ጥያቄ በሰላምና በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ መፍታት ይቻላል ብለን ነው የመጣነው፡፡ ሰላማዊ የትግል ሥልት የመረጥነው ለዚህ ነው፡፡ የሰሜኑ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት የፖለቲካ ግጭቱና ልዩነቱ በሰላም መፈታት ይችላል ብለን ልዩነቶች በውይይት ዕልባት እንዲያገኙ ስንጠይቅ ነበር፡፡ መወነጃጀሉ ቆሞ ወደ ውይይት እንዲመጣ ስንጠይቅ ቆይተናል፡፡ የሰሜን ዕዝ ስለተመታ ነው ጦርነቱ የተጀመረው ይባላል፡፡ ብዙ መወነጃጀሎች ይሰማሉ፡፡ ነገር ግን ከጦርነቱ በፊት ያየናቸው በሙሉ ግጭቱን አይቀሬ የሚያደርጉ ለጦርነት የሚገፋፉ ነገሮች ነበሩ ከሁለቱም ወገኖች፡፡ በሁሉም በኩል ለጦርነት የመዘጋጀት እንቅስቃሴ ነበር፡፡ ሕወሓት ከመቀደም ልቅደም ብሎ የሰሜን ዕዝን ማጥቃቱ ብዙም ተወቃሽ አያደርገውም፡፡ ከተገባም በኋላ ጦርነቱ መፍትሔ እንደማይሆንና ቆሞ ችግሩ በሰላም ዕልባት እንዲያገኝ ስንጠይቅ ነበር፡፡ በኦሮሚያም ቢሆን ይህንኑ ነው የምንለው፡፡ በሰሜን ያ ሁሉ ዕልቂት ከተፈጸመ በኋላ በሰላም ነው የተቋጨው፡፡ ስለዚህ በሰሜን ጦርነት መፍትሔ ካልሆነ በኦሮሚያ ውስጥስ እንዴት መፍትሔ ሊሆን ይችላል? በሰሜን ችግሩን ለመፍታት የተኬደበት መንገድ ኦሮሚያ ውስጥስ ለምንድነው የማይተገበረው? መንግሥት ፍርደ ገምድልነቱን ያቁም ነው የምንለው፡፡ መንግሥት በሰሜኑ ከተካሄደው ጦርነት ምንም ማትረፍ እንደማይቻል ዓይቶታል፡፡ በኦሮሚያ ያለውን ዕልቂትም በሰላም የማያቆምበት ሁኔታ አይታየንም፡፡

ሪፖርተር፡- ሽምግልና አልተሞከረውምይ? በባህላዊ ዕርቅ ተብሎ ታዋቂ የኦሮሞ ፖለቲከኞችና አባ ገዳዎች ወደ ወለጋ ሄደው አልነበረም?

አቶ በቴ፡- መንግሥት በሰሜንም ብዙ ርቀት ሄጃለሁ ሲል ነበር፡፡ ሽምግልና የሄዱ ሰዎች ሳይቀር ለጦርነት ሲዘምቱ በታሪክ ታዝበናል፡፡ ወደ ወለጋም የሄዱት እምቢተኝነት መርጧል ብለው ነው የተመለሱት፡፡ ነገር ግን በላከው የሽማግሌ ብዛት የሰላም ፍላጎት አይለካም፡፡ አንዴ አድርጌዋለሁና ከእኔ አልቀረም በሚል ግብዝ ምክንያት የሰላም ጥረትን አትተወውም፡፡ ሰላማዊ መፍትሔን ለማፈላለግ ሁሌም ልትተጋ  ይገባል፡፡ ነገር ግን በኦሮሚያ እነ ጃዋር ሄደው የተወሰነ ትጥቅ ማስፈታት ችለው ነበር፡፡ ሆኖም የፀጥታ ሥጋት አለ በሚል ምክንያት ሽማግሌዎቹንም በአንድ ማቆያ አጉረው ነው ያቆዩዋቸው፡፡ የታጠቀውን ኃይል ወደ ካምፕ አስገብቶ ተሃድሶ ሰጥቶ ወደ ሰላማዊ መንገድ የማሰማራት ሥራው በተገባው ቃል መሠረት አልተከናወነም፡፡ ጦላይና ወሊሶ ካምፕ አስገብተህና ተሃድሶ ሰጥተህ ሜዳ ላይ የምትበትን ከሆነ ግን ሌላውስ ምን ዋስትና አለው? መንግሥት ከገባው ቃል መደረግ ያለበትን ጥቂቱን እንኳ ባለማድረጉ ብዙዎች ወደ ጫካ ተመልሰው እንዲገቡና ነገሩ እንዲባባስ ተደርጓል፡፡

No comments:

Post a Comment