የኦህዴድ ምስረታና ከህወሓት ጋር የተደረገ ስምምነት፤
በ ሀብታሙ አሰፋ
በ1981 ዓ.ም በሕወሓትና በኢህዴን ጥምረት ኢህአዴግ ከመመስረቱ በፊት ኦነግን ግንባሩን ተቀላቅሎ ደርግን በጋራ ለመዋጋትና ከድል በኃላ ለኦሮሞም ሆነ ለሌሎችም ብሄር ብሄረሰቦች ሪፈረንደም ተሰጥቶ ህዝቡ ኦነግ እንደሚመኘዉ ነፃ የኦሮሚያ ሪፐብሊክ መንግስትን የመመስረት ወይም ኢህአዴግ እንደሚፈልገዉ በኢትዮጵያ አንድነት ጥላ ስር የኦሮሞ ህዝብ የራሱን እድል በራሱ የመወሰን ዲሞክራሲያዊ መብቱ እንዲጠበቅለት ከሚሉት አማራጮች አንዱን በካርዱ ይመርጣል፤ ህዝብ በሚወስነዉ ጉዳይ ኦነግና ኢህአዴግ ጫካ ዉስጥ በሀሳብ መለያየቱ ትርጉም ስለሌለዉ አንድ ግንባር ሆነን ደርግን እንዋጋ የሚል ጥያቄ የኢህዴን ከፍተኛ አመራር በነበሩት በእነ ኢብራሂም መልካ በኩል ከ1981 በፊት የኦነግ ፅ/ቤት ወዳለበት ሱዳን ድረስ እየሄዱ ኦነግን ለማግባባት ጥረት አድርገዋል፡፡ኦነግ የሚመሰረተዉን የኢህአዴግ ግንባር ላለመቀላቀል የሚያቀርባቸዉ ምክንያቶች ሁለት ነበሩ፡፡ አንደኛዉ ኦሮምያን ከደርግ አገዛዝ በራሴ ሰራዊት ተዋግቼ ነፃ አወጣለሁ፤ የሰሜኖች ድጋፍ አያስፈልገኝም ሲሆን፤ሁለተኛዉ ደግሞ የኢትዮጵያ ገዢ መደቦች ምንጫቸዉ ከሰሜን ስለሆነ ከገዢዎች ጋር ግንባር መፍጠር አንፈልግም የሚል ነዉ፡፡እንደዉም ግንባር እንፍጠር የሚሏቸዉ እነ ኢብራሂም መልካ ኦሮሞዎች ስለሆኑ ለምን ኦነግን ተቀላቅላችሁ አብረን አንታገልም የሚል ጥያቄ እንደቀልድ ጣል ያደርጉ ነበር፡፡
እናም ኦነግ ግንባሩን አልቀላቀልም ማለቱ ቁርጥ ሲሆን በ1981 ዓ.ም በሕወሓትና በኢህዴን ጥምረት ኢህአዴግ ተመሰረተ፡፡በኢህዴን ዉስጥ ደርግን ሲታገሉ የነበሩ የኦሮሞ ታጋዮች እነ ኢብራሂም መልካ፤ጀነራል ባጫ ደበሌ፤አባዱላ ገመዳ፤ኩማ ደመቅሳ፤ጌታቸዉ በዳኔ (badhane)፤ ዮናታን ዲቢሳ (dhiphisa)፣ በቀለ Badhaadha፣ዲማ ጉርሜሣ እና ሌሎችም ከኢህአዴግ ምስረታ በኃላ የኦህዴድን ፕሮግራም ረቂቅ አዘጋጅተዉ ትግራይ አዴት ሄደዉ ሲወያዩበት ከቆዩ በኃላ መጋቢት ወር 1982 ዓ.ም ኦህዴድ በይፋ ተመሰረተ፤ የኢህአዴግም አባል ሆነ፡፡ለኦሮሞ ሕዝብ አማራጭ የሚሆን ፕሮግራም አቀረበ፤ የኦሮሞ ህዝብ ቋንቋዉ ባህሉና ማንነቱ ተከብሮ የራሱን ጉዳይ በራሱ እያስተዳደረ ከሌሎች ብሔር ብሄረሰቦች ጋር ተከባብሮና ተዋዶ በኢትዮጵያ አንድነት ጥላ ስር አብሮ ቢኖር አንድነቱ ከሚፈጥረዉ ሰፊ ገበያ የኦሮሞ ህዝብ ተጠቃሚ ይሆናል ብሎ ያምናል ኦህዴድ፡፡
በሌላዉ ተቃራኒ ጫፍ የቆመዉ ኦነግ ደግሞ ኦሮሞ ከኢትዮጵያ ተገንትሎ ነፃ የኦሮሚያ ሪፐብሊክ መንግስትን የመመስረት አማራጭ ለኦሮሞ ህዝብ አቅርቧል፡፡ኦነግ ግን ልክ እንደ ቁማርተኛ ጎፈርም ዘዉድም ብሎ ቁማሩን ለመቆመርና ለማሸነፍ ፈለገ፤ለኦሮሞ ህዝብ ሪፈረንደም ተሰጥቶ ነፃ የኦሮሚያ ሪፐብሊክ መንግስትን መመስረት ከወሰነ ኦነግ የኦሮሞ ነፃ መንግስትን ሊመራ፤በተቃራኒዉ የኦሮሞ ህዝብ ኢትዮጵያ ዉስጥ ካሉ ብሄር ብሄረሰቦች ጋር በአንድነት መኖርን ከመረጠ ኦነግ ኢትዮጵያን በበላይነት ለመምራት ቋመጠና የምታገለዉ የኦሮሞ ህዝብ ሪፈረንደም ተሰጥቶት የራሱን እድል በራሱ እንዲወስን ለማስቻል ነዉ አለ፡፡ሪፈረንደሙ ይሰጥ እንጂ የኦሮሞ ህዝብ ነፃ መንግስት ወይም አንድነት ቢወስን ለኦነግ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ሆኑ፡፡በሰኔ ወር 1984 ዓ.ም ምርጫ ከመካሄዱ በፊት "ፎረም 84" የሚባል ተቋም የፖለቲካ ፓርቲዎችን በሙሉ እየሰበሰበ ለሕዝብ ፕሮግራማቸውን የሚያስተዋውቁበት መድረክ አመቻችቶ ነበር። በዚህ መድረክ ላይ ኢህአዴግን ጨምሮ በወቅቱ የነበሩ ሁሉም ፓርቲዎች እየተገኙ ፕሮግራማቸውን ያስተዋውቁ ነበር።በመድረኩ ላይ የኦሮሞ እስላማዊ ነፃነት ግንባር (IFLO) የፖለቲካ ፕሮግራሜ "በእስላማዊ ሸሪዓ ሕግ የምትመራ ነፃ የኦሮሚያ መንግስት መመስረት" መሆኑን ገለፀ ፣ኦህዴድ "በኢትዮጵያ አንድነት ጥላ ስር የኦሮሞን የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ማስከበር" መሆኑን ገለፀ፣ኦነግ ደግሞ የምታገለው "የኦሮሞ ሕዝብን የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ለማስከበር ነው" አለ።እንደ IFLO በግልፅ "በእስላማዊ ሸሪዓ ሕግ የምትመራ ነፃ የኦሮሚያ መንግስት መመስረት" ነው ወይም እንደ ኦህዴድ "የኦሮሞ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ መብቱ ተከብሮ ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በኢትዮጵያ ጥላ ስር በአንድነት መኖር ነው " አላለም።የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት የመገንጠል እና የአንድነት ፅንሰ ሀሣብ በውስጡ ስለያዘ ኦነግ መገንጠል ወይም አንድነት እንደሚፈልግ በፕሮግራሙ በግልፅ ስላላስቀመጠ በወቅቱ በፎረም 84 መድረክ ላይ የኦነግ የፖለቲካ ፕሮግራም ግልፅ አይደለም መባሉን አስታውሳለሁ ።
ኦህዴድ ደግሞ ግልፅ የሆነ የፖለቲካ አቋም ይዞ የኦሮሞ ህዝብም ሆነ የሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ጥያቄ በሪፈረንደም መፈታት ቢኖርበትም ለኦሮሞ ህዝብ የሚጠቅመዉ ከኢትዮጵያ መገንጠል ሳይሆን መብቱ ተከብሮ ከሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ጋር በአንድነት በመኖር የበለጠ ተጠቃሚ የሚያደርገዉ ቢሆንም አንድነቱም ቢሆን ኦህዴድ-ኢህአዴግ ስለፈለጉ በሀይል ሊጫንበት ስለማይገባ የሚፈልገዉን በሪፈረንደም ይወስን የሚል አቋም ተያዘ፡፡
ኦህዴድ የኦሮሞ ህዝብ ነፃ መንግስት መመስረት ወይም አንድነትን መፈለጉ የሚረጋገጠዉ በህዝበ ዉሳኔ ወይም በሪፈረንደም ስለሆነ ከምርጫ 84 በፊት ጉዳዩን በኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ደረጃ ተወያይቶ ከኤርትራ ሪፈረንደም ጋር ተያይዞ የኦሮሞ ህዝብም የሚፈልገዉን ለመለየት በኦሮምያ ክልል ዉይይት ከህዝቡ ጋር እንዲካሄድ ተወስኖ ሰፊ ዉይይት ተካሂዶ እኔም የድሬዳዋን ከ24 የከተማ ቀበሌዎች የተወከሉ ኦሮሞዎችን አወያይቼ ነበር፡፡ በዉይይቱ የተካፈሉ የድሬዳዋም ሆነ የኦሮምያ ክልል የከተማ ነዋሪ ኦሮሞዎች አስተያየቶች ለኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ሪፖርት ቀረበ፤በሪፖርቱ ዉጤት መሰረት የኦሮሞ ህዝብ ሪፈረንደም ተሰቶት ነፃ የኦሮምያ መንግስት መመስረትም ይሁን በኢትዮጵያ አንድነት ጥላ ስር ለመቀጠል መወሰን እንደሚፈልግ ተረጋገጠ፡፡
ይሁን እንጂ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ በሪፖርቱ ዉጤት ላይ ባደረገዉ ዉይይት የኦህዴድ ከፍተኛና መካከለኛ ካድሬ ያወያየዉ የየከተማዉን ተወካይ ስለሆነና የየከተማዉ ኦሮሞ ደግሞ የኦነግ ደጋፊ በመሆኑና ኦህዴድ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ መርህ መሰረት ወገንተኛነቱ ለገጠሩ አርሶ አደር ስለሆነና ሰፊዉ የኦሮሞ ህዝብ አርሶ አደር ስለሆነ በድጋሚ ገጠር ያለዉን የኦሮሞ አርሶአደር አወያዩ የሚል ተልዕኮ ወረደ፤በወቅቱ ይህንን ሀሳብ ከሚያራምዱት የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ዉስጥ ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ተጠቃሽ ናቸዉ፡፡
ተልዕኮዉ የተሰጠን የኦህዴድ ከፍተኛኛ መካከለኛ ካድሬዎች የገጠሩንም አርሶ አደር አወያየን፤ዉጤቱ የከተማዉም ሆነ የገጠሩ የኦሮሞ አርሶ አደር ሪፈረንደም እንደሚፈልግ በድጋሚ አረጋገጠ፡፡
ከዚህ በኃላ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ የኦሮሞ ህዝብ ልክ እንደ ኤርትራ ህዝብ ሪፈረንደም እንደሚፈልግ ወስኖ አጀንዳዉ ለኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ቀርቦ ዉሳኔ እንዲያገኝ ስምምነት ላይ ተደረሰ፡፡የኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ እንደ ነገ ሊሰበሰብ እንደዛሬ አንድ አስገራሚ ክስተት ተፈጠረ፤ጉዳዩን ለኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ማቅረብ ያለበት የወቅቱ የኦህዴድ ሊቀመንበር የነበረዉ አቶ ኩማ ደመቅሳ በሀሳቡ ላይ ብስማማም እኔ አላቀርብም አለ፤እናም የወቅቱ የኦህዴድ ፀሐፊ የነበሩት አቶ ኢብራሂም መልካ እንዲያቀርቡ ተወስኖ የኦሮሞ ህዝብ የሪፈረንደም ጥያቄ ለኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ቀረበ፡፡የኦሮሞ ጥያቄ በሪፈረንደም መፈታት እንዳለበት ኢህአዴግ ገና ደርግ ሳይወድቅ ጫካ በነበረበት ጊዜ የወሰነዉ ጉዳይ ነዉ አሁን ለአፈፃፀም ቀረበ እንጂ ጥያቄዉ አዲስና ዱብዕዳ አልነበረም፡፡ ሕወሃትም ከደርግ ጋር የታገለው የትግራይን ሕዝብ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብቱን ለማስከበር ነበር፣ነገርግን ጫካ የተወሰነን ዉሳኔ ዛሬ የሚኒሊክ ቤተመንግስት ዉስጥ ተገብቶ ለማፅናት ጉሮሮ ዉስጥ እንደተሰነቀረ አጥንት አስቸጋሪ ሆነ፡፡ሕወሃት ስልጣን ላይ ለመቆየት ሲል የራስን እድል በራስ ከመወሰን መብት ሣይንሳዊ አፈታት ጋር በተቃርኖ ቆመ።
የኢህአዴጉ ሊቀመንበር መለስ በተካነበት የመከፋፈል ጥበብ “በኢብራሂም መልካ ሀሳብ ላይ ሌሎቻችሁ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ያላችሁን ሀሳብ መስማት እንፈልጋለን አለ”፡፡
የኢህአዴጉ ሊቀመንበር መለስ በተካነበት የመከፋፈል ጥበብ “በኢብራሂም መልካ ሀሳብ ላይ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ያላችሁን ሀሳብ መስማት እንፈልጋለን አለ”፡፡ብለን
ዶክተር ነጋሶ እጁን አወጣ፤“አንተ ድሮም የኦነግ አባል መሆንህን እያወቅን ነዉ የኦህዴድ አባል ያደረግንህና አመለካከትህን ስለምናዉቀዉ የመናገር እድሉን አልሰጥህም” አለ መለስ፡፡
ቀጥሎ ሀሰን አሊ እና ኩማ ደመቅሳ በየተራ እጅ አዉጥተዉ ከሞላ ጎደል የሚከተለውን ተመሳሳይ ሀሳብ ተናገሩ ፣“በኦሮሚያ ወታደራዊ አገዛዝ ስለሰፈነ የኦሮሞ ህዝብ እየታሰረ ስለሆነ ይህ ችግር እንዲፈታልን“ ብለዉ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ በቃለ ጉባኤ ተፈራርሞ የወሰነዉን የኦሮሞ ህዝብ የሪፈረንደም ጥያቄ አዉርደዉ ከኦሮሞ መታሰር ጋር ለመያያዝ ሞከሩ፡፡ችግሩ የተፈጠረዉ ኩማ ደመቅሳ እኔ አላቀርብም ባለ ጊዜ ነበረ፡፡
የኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴም ኦህዴድ ኢብራሂም መልካን እንዲገመግም ብሎ ስብሰባዉን አጠናቀቀ፤በዚያዉ ሰሞን መለስ ኢብራሂም መልካን ቤተመንግስት አስጠራና “ኦነግ የመገንጠል አቋሙን ካልቀየረ ከሽግግር መንግስቱ ልናባርረዉ ወስነናል” ይለዋል፡፡የመለስ አነጋገር በተዘዋዋሪ መንገድ ለኦሮሞ ህዝብ ሪፈረንደም አንሰጥም ማለቱ ነበር፡፡ የመለስ አሽሙር የገባዉ ኢብራሂም መልካም “የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ ካልተፈታ አሁን ላይ ሆኜ መቼ ኢህአዴግ እንደሚወድቅ መገመት ቢያስቸግረኝም መዉደቃችሁ ግን አይቀርም” ብሎ እንቅጩን ነግሮት ተለያዩ፡፡ኢብራሂም መልካም ከ1986 ዓ.ም ጀምሮ ከኦህዴድ-ኢህአዴግ አባልነት እራሱን አገለለ፡፡ ሕወሃት በመሳሪያ ያገኘሁትን ስልጣን በሕዝበ ዉሳኔና በምርጫ አላስረክብም ብሎ ከደርግ ዉድቀት በኃላ በኢትዮጵያ ሕግ የሚገዛዉ ዲሞክራሲያዊ መንግስትና ሀገር የመገንባት እድልን አመከነ፡፡
መጋቢት ወር 1984 ዓ.ም በሰኔ ወር ሊካሔድ በተወሰነው ሀገራዊ ምርጫና ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለመገንባትና በሰላም ጉዳዮች ላይ ለመወያየት የኢህአዴግ እና የኦነግ ካድሬዎች አዲስአበባ ተሰብስበን ነበር።መድረኩን የሚመሩት በኢህአዴግ በኩል የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበሩት አቶ ተወልደ ሲሆኑ፣በኦነግ በኩል አቶ ሌንጮ ለታ ነበሩ ።በሀገሪቱ ሰላምና ዲሞክራሲን ማስፈን እንዳለብንና በሰኔ ወር የሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ ሁለቱ ፓርቲዎች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ተስማምተን ስብሰባው ተጠናቀቀ ።
ሰኔ 14 ቀን 1984 ዓ.ም ሊካሔድ የታቀደው ሀገራዊ ምርጫ 10 ቀናቶች ብቻ ሲቀረው ደግሞ በኮሚኒኬሽን ዘርፍ የሚሰሩ ከፍተኛ የኢህአዴግ ካድሬዎች የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ በነበሩት በአቶ አለምሰገድ ገብረአምላክ ሰብሳቢነት ተሰበሰቡና አቶ አለምሰገድ "በደም ያገኘነውን ስልጣን በካርድ አናስረክብም"፣"በኦሮሚያ በቂ ዝግጅት አላደረግንም ፣ኦህዴድ መላውን የኦሮሞን ሕዝብ ከጎኑ ለማሰለፍ በቂ ጊዜ አላገኘም ፣በምርጫ ስም ኦሮሚያን ለኦነግ አናስረክብም፣ስለዚህ ኦነግ ከምርጫው እራሱን ማግለል አለበት ካልሆነ ኦነግ የሚያሸንፍበት ምርጫ ይሰረዛል " በማለት "ስልጣን ከመሣሪያ አፈሙዝ እንጂ ከምርጫ ኮሮጆ ወይም ሣጥን እንደማይወጣ ኢህአዴግ በማያሻማ ቋንቋ አረጋገጠ።
በወቅቱ ኢህአዴግ በተለይ ደግሞ የኢህአዴግ ቀላሽ የሆነው ሕወሓት ኦነግን በተመለከተ በሁለት ፅንፍ በወጡ መንታ መንገዶች ወይም አማራጮች ላይ ተከፈሉ።
የእነ መለስ ቡድን ኦነግን ማታለልና የኢህአዴግ አባል ማድረግና ኦህዴድን ማፍረስ ሲሆን፣ የእነ ተወልደና አለምሰገድ ቡድን ኦነግን በሀይል ከቻርተሩ ማስወጣት የሚለው ነው ።
በመለስ የሚመራው የመለስ ቡድን ኦነግን ለማታለል ከኦነግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ሣይሆን አቶ ሌንጮ ለታን ለብቻው ቤተመንግስት እየጠራ ኦነግን ከኢህአዴግ ጋር ለማቀራረብ ተደጋጋሚ ውይይት አድርጓል ።
በሌላ በኩል በአንድ የኢህአዴግ ስብሰባ ላይ አለምሰገድ “ኦህዴድ የኦሮሞ ህዝብ ድጋፍ ስለሌለዉ ከኢህአዴግ ይዉጣ” ይላል፤ ኢብራሂም መልካ “አሁኑኑ አድርጉት፤ እንደዉም ከናንተ መገላገል ለኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ መመለስ መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል” ይለዋል፡፡ አባዱላ ገመዳ ይከተልና አለምሰገድን “አንተ ማን ቀጣሪና አባራሪ አደረገህ? ያለአቅምህ አትንጠራራ” ብሎት ነበር፡፡
በእነ ተወልደ የሚመራው ቡድን ደግሞ "ውፃእ አይትበሎ፣ ከምዝወፅእ ግበሮ"--"ውጣ አትበለው ፣እንዲወጣ አድርገው" በሚለው መርሀቸው መሠረት የኦነግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን ትቶ በታችኛው እርከን ያሉ የኦነግ ከፍተኛና መካከለኛ ካድሬዎችን መግደል፣በኦሮሚያ ውስጥ በፊንፊኔ ጉለሌ ከሚገኘው የኦነግ ፅ/ቤት በስተቀር ሌሎቹን መዝጋት ጀምሮ ነበር።
የመለስና የእነ ተወልደ ቡድን በአቋም የተለያዩ ይምሰሉ እንጂ ውስጥ ለውስጥ ተስማምተው የማታለሉንም የማባረሩንም ዘመቻ በተናበበ መልኩ ኦነግ ላይ ከፍተውት ነበረ።
በመጨረሻም የማታለልና የማባረር ዘመቻው ተሣክቶ ኦነግ ከምርጫ 84 እራሱን ማግለሉን በተታለለው በኦነግ ዋና ፀሐፊ በአቶ ሌንጮ ለታ በኩል መግለጫ ተሰጠ። መግለጫው በኢህአዴግ መንደር እፎይታና ደስታ ሲፈጥር ከኦነግ ማዕከላዊ ኮሚቴ በስተቀር በኦነግ ከፍተኛ ፣ መካከለኛ ፣ ጀማሪ ካድሬዎች እና በተራው የኦነግ ደጋፊ ኦሮሞዎች ላይ ሰቆቃ፣እስራትና ስደትን ፈጠረ።
ኢህአዴግ አዲስአበባን ከመያዙ አንድ ወር በፊት በሚያዝያ ወር 1983 ዓ.ም በጫካ ውስጥ በተደረገ ስብሰባ የመድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲን በመርህ ደረጃ ለመቀበል ወስኖ ደርግ ከወደቀ በኃላ የኢህአዴግን የፖለቲካ፣የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ፕሮግራም ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 1987 ዓ.ም ሁሉም የኢህአዴግ አባል ታጠቅ በሚባለው የደርግ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ካምፕ ለሶስት ወር በሚቆይ የተለያየ ዙር ስልጠና የኢህአዴግ የፖለቲካ ፕሮግራም መድብለ ፓርቲን እንደሚቀበልና የኢኮኖሚ ፕሮግራሙ ደግሞ ነፃ ገበያ እንደሆነና የማህበራዊ ዘርፍ ፕሮግራሙ ለአርሶ አደሩ እንደሚያደላ በግልፅ ወሰነ።
ነገር ግን እኔም ከጥቅምት እስከ ታህሳስ ወር 1986 ዓ.ም በተሣተፍኩበት የታጠቅ ስልጠና "ብንሸነፍ ስልጣን እናስረክባለን ወይ?"የሚል ጥያቄ በየቡድኑ እንድንወያይ ቀርቦ ነበር ።በወቅቱ እኔ ጨለንቆ የሚባል ቡድን ፀሐፊ ስሆን ቡድኗ የድሬዳዋ ፣የሐረር ፣የምስራቅ እና ምዕራብ ሐረርጌ የኦህዴድ ካድሬዎችና አስተዳዳሪዎችን የያዘች ቡድን ናት።በዋናው መድረክ ጥያቄው "ብንሸነፍ ስልጣን እናስረክባለን ወይ?ለውይይት ሲቀርብ መድብለ ፓርቲን ተቀብለን ስናበቃ በዚህ ጥያቄ ላይ መወያየቱ ለምን አስፈለገ ብዬ የሞገትኩት እኔ ነበርኩ።ይሁን እንጂ ለውይይት የሚቀርቡ ጥያቄዎች የሚላኩት ከኢህአዴግ ስለሆነ የስልጠና ካምፑ አስተባባሪዎች እንደወረደ ለሰልጣኙ ማቅረብ እንጂ መለወጥ ስለማይችሉ ሁሉም ሰልጣኝ ለሊቱን በጥያቄው ላይ ተወያይቶ በየቡድኑ ፀሐፊዎች ጠዋት ለዋናው መድረክ ሪፖርት ይቀርባል።በአጋጣሚ ሁሉም ቡድን "ብንሸነፍ ስልጣን እናስረክባለን"ብሎ ወሰነ።ለዚህና ለሌሎችም ጥያቄዎች ቅዳሜና እሁድ ታጠቅ እየመጡ ማብራሪያ የሚሰጡት የኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት መካከል ለዚህና ለሌሎችም ጥያቄዎች ማብራሪያ ሊሰጡ የመጡት የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር የነበሩት አቶ ስዩም መስፍን "ለመሆኑ ማስረከብ ሲባል ትርጉሙ ገብቷችኋል ወይ?ብለው በጥያቄ ጀምረው "ከተሸነፍን ስልጣን የምናስረክበው ከመለስ ጀምሮ እኛ ሚኒስትሮቹ ብቻ እንዳይመስላችሁ፣ እስከ ቀበሌ ድረስ ያለው የኢህአዴግ ካድሬና ሹመኛ ሁሉ ስልጣን ለተመረጠው ተቃዋሚ ፓርቲ ያስረክባል ፣ስልጣን ካስረከብን በኋላ ለናንተ ካድሬዎች እና ሹመኞች ኢህአዴግ የሚከፍለው ደመወዝ የለውም"ብለው አባሉን በሆዱ ለመግዛት ሲያስቡ ኢህአዴግ እና ዲሞክራሲ የማይገናኙ የሁለት አለም ሰዎች መሆናቸውን አስረግጠው ነገሩን ።
በ1985 ዓ.ም ኦህዴድ ከኢህአዴግ ይዉጣ በተባለ ሰሞን የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ተሰብስቦ በሀሳቡ ዙሪያ ተወያየ “አሁን ያለዉ የኦሮሞ ምሁር፤ባለሀብት፤ቄስና ሼክ የኦነግ አባልና ደጋፊ ነዉ ፤ኦህዴድ የአሁኑ ያረጀ ያፈጀ ትዉልድ ፓርቲ ሳይሆን የመጪዉ ወይም የነገዉ ዘመን ትዉልድ ፓርቲ (The new generation party) ነዉ” የሚል አቋም ተይዞ በወቅቱ ኦህዴድን ይከተሉ የነበሩት ታዳጊ ወጣቶች ላይ ለመስራት ተወሰነ፡፡ በታጠቅና በሁርሶ ወታደራዊ ማሰልጠኛዎች በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን በማሰልጠን ግማሹን ወደ መከላከያ የተቀረዉን ወደ ኦህዴድ ካድሬነት በመመደብ በኦሮሚያ ከፍተኛ ለዉጥ እንዲመጣ ተደርጓል፡፡ መጪዉ አዲሱ ትዉልድ በኦሮሞ መብቶችና ጥቅሞች ላይ ከአሁኑ ወይም ከአሮጌዉ ትዉልድ በላይ አምርሮ እንደሚታገል ተገምቶ ኦህዴድ በወጣቱ ላይ ሰርቶ ዛሬ ቄሮና ቀሬን አስተምሮ በሀገራችን ለመጣዉ ለዉጥ ከፍተኛዉን ሚና ተጫዉቶ ሕወሃትን መቀሌ አስገብቷል፡፡ ኦህዴድ ከኢህአዴግ ይዉጣ ሲል የነበረዉን ሕወሃት እራሱን ከኢህአዴግ አስወጥቶ መቀሌ ያስገባዉ በኦህዴድ የተመራዉ የኦሮሞ ህዝብ አመፅ ነዉ፡፡ ሕወሃት ከጫካ ጀምሮ ስልጣን ይዞ ለ27 አመታት ሀገር ሲያስዳድር አንድም ጊዜ ተሳስቶ ዲሞክራሲያዊ ሆኖ አያዉቅም፤የኢትዮጵያ ህዝብ በአገዛዙ ተማሮ ባዶ እጁን አደባባይ ወጥቶ ተቃዉሞ ሲያሰማ “በደም ያገኘነዉን ስልጣን በመንገድ ላይ አመፅ አናስረክብም” በማለት በስልጣኑ ላይ ለመቆየት ሲል በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን በጥይት ደብድቦ ገድሏል፤የህዝብ ተቃዉሞ እየጠነከረበት ሲሄድ ደግሞ ስልጣኑን ለቆ ወደ መቀሌ ከሸሸም በኃላ እንደገና ወደ ስልጣን ለመመለስ የትግራይን ወጣቶች ለጦርነት አዘጋጅቶ እራሱ በከፈተዉ ጦርነት ለሚሊዮኖች እልቂትና መፈናቀል ምክንያት ሆኗል፡፡
ማጠቃለያ ፦
ይህ ከክፍል 1 እስከ 3 የቀረበው ፅሁፍ አላማ የሚከተሉትን ጭብጦች ለአንባቢያን ግልፅ ለማድረግ ነው ።
1/ኢህአዴግ በተለይም ሕወሃት ለይስሙላ የመድበለ ፓርቲ ዲሞክራሲን እቀበላለሁ ቢልም በተግባር ግን "በደም ያገኘነውን ስልጣን በምርጫ ካርድ አናስረክብም፣በምርጫ ከተሸነፍን ስልጣን ለአሸናፊው ተቃዋሚ ፓርቲ አናስረክብም " የሚል የዲሞክራሲ ፀር የሆነ ግንባር ነው ። የንጉሱ፣የደርግና የኢህአዴግ ስርአቶች ለኢትዮጵያ ሕዝብ የዲሞክራሲ ጥያቄውን አልመለሱለትም።በመሆኑም የብልፅግና ፓርቲ የሕዝቡን የዲሞክራሲ ጥያቄ ለመመለስ ተስፋ ሰጪ ጥረቶችን እያደረገ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ።
2/ ኦህዴድ ከተመሰረተበት ከመጋቢት ወር 1982 ዓ.ም ጀምሮ የኦሮሞ ሕዝብን ጥያቄዎች ለመመለስ ያደረገውን ትግልና ያስመዘገባቸውን ድሎች እውቅና መስጠት ይገባል።
ኦህዴድ በእሣት ውስጥ ያለፈ ድርጅት ነው ።በአንድ በኩል በሽግግር መንግስቱ ዘመን ኦነግ በከፈተበት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ "ኦህዴድ የሕወሃት ተላላኪ ነው "ሲባል፣በሌላ በኩል ደግሞ "ኦህዴድ የኦሮሞ ህዝብ ድጋፍ ስለሌለው ከኢህአዴግ አባልነት ይውጣ "ሲል የነበረውን ሕወሃት እየታገለ "የነገው ዘመን ድርጅት" መሆኑን አምኖ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ወጣቶችን መልምሎ ወታደራዊና ፓለቲካዊ ስልጠና በመስጠት እራሱን ካጠናከረ በኋላ "ኦህዴድ ከኢህአዴግ ይውጣ ሲል የነበረውን ሕወሃት እራሱን ከቤተመንግስት አስወጥቶ የብልፅግና የለውጥ መንግስት እንዲመሰረት ከፍተኛውን አስተዋጽኦ ማድረጉ መዘንጋት የለበትም።ለኦሮሞ ሕዝብ መብት መከበር በትጥቅና በሰላማዊ መንገድ እንታገላለን ካሉት ከእነ ኦነግ፣ኦእነግ(ጃራ)፣ከኦፌኮና ከመሳሰሉት በላቀ ሁኔታ የኦሮሞን ሕዝብ መብት ያስከበረ ድርጅት ኦህዴድ ነው ።ቀሪ የኦሮሞን ሕዝብ መብትም የሚያስከብረው እራሱ የኦሮሞ ሕዝብና እና የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ በሚያደርጉት የተቀናጀ ትግል መሆኑ መታወቅ አለበት ።
3/የብሔር ብሔረሰቦች የራስን እድል በራስ የመወሰን መብትን ለማስከበር የተዋቀረው ፌዴራሊዝም ዲሞክራሲያዊ ሆኖ መቀጠል አለበት።
4/ ሕወሃት ”በደም ያገኘሁትን ስልጣን በምርጫ ካርድ አላስረክብም“ የሚለዉን ኢዲሞክራሲያዊ አቋሙን ለዉጦ በትግራይ ክልል የዲሞክራሲ ባህልን ገንብቶ ”ስልጣን ከመሳሪያ አፈሙዝ ሳይሆን ከምርጫ ኮሮጆ ወይም ሳጥን“ እንዲወጣ ያድርግ፡፡ካልሆነ ድርጅቱ እንደበፊቱ የሰዉ አንገት እየቀላ ለመኖር ከወሰነ ህልዉናዉ ከታሪክ መዝገብ ይሰረዛል፡፡
No comments:
Post a Comment