Friday, February 22, 2013

የመንግስታት የእርስ በእርስ ግንኙነት በኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም


 1 መግቢያ
የመንግሥታት እርስ በእርስ ግንኙነት በሕገመንግሥታችን መግቢያ ላይ የተቀመጠውን አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ በጋራ ለመግንባት በማደረገው ሂደት ውስጥ አንደመሣሪያ ያገለግላል ይኸውም በፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች እንዲሁም በየእርከኑ ባሉ ተቋማት መካከል ያለውን ትስስርና መስተጋብር የሚጠናከርበት ሂደት ነው፡፡
በሕገ-መንግሥቱ የተደነገገው የክልሎችና የፌዴራል መንግሥቱ የሥልጣን ወሰን እንደተጠበቀ ሆኖ በአጠቃላይ በሪፑብሊኩ ውስጥ በትብብር የሚከናወኑ የፖሊሱ የስታንዳርድ እንዲሁም የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ግንባታ ሥራዎችን በተሻለ ሁኔታ መተግበር ያስችላል፡፡
በተጨማሪም መሠረታዊ የሕገ-መንግስቱ ድንጋጌዎች መሬት እንዲነኩ ከማድረጉም በላይ የፌዴራል ሥርዓቱ ጠንካራ መሠረት ላይ እንዲገነባ ያስችላል፡፡
በዚህ መሠረት የፌዴራሊዝም መርሆዎችን በመከተል “self Rule and shored rule” በተለይ በጠበቀ ሁኔታ በትብብር ሥርዓቱን ለመገንባት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፍጠር ያስችላል፡፡
ከዚህ ቀደም በፌዴራልና በክልል መንግሰታት መካከል የተጀመሩ የእርስ በእርስ ግንኙት መድረኮችን የበለጠ ተቋማዊ ከማድረግ በተጨማሪ ሌሎች መድረኮች የሚፈጠሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡
በመሆኑም የco-operative Federation ፅንሰ ሐሳብ መሠረት ያደረገ ሀገራዊ የጋራ ጉዳዮች የሚመክርባቸውን መድረኮች ማቋቋም ያስፈልጋል፡፡




እነዚህም
·         በአስፈፃሚው መካከል፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ እና በክልል ርዕሳነ መንግሥት እንዲሁም በየሴክተሩ በሚደራጁ ኮንፍረንሶች ፎረሞች የሚደራጁ ሆነው አስገዳጅነት በሌለውና በሕገመንግስቱ የተቀመጡ የሥልጣን ወሰኖችን በመጠበቅ ለጋራ ሀገራዊ ጉዳይ የሚመክሩበትን መድረክ ማደራጀት ይቻላል፡፡
·         ይሀንን ተቋማዊ አሠራር ለማምጣት ሁሉም የሚሳተፉበት የግንዛቤ መፍጠሪያና የመግባቢያ መድረኮች አስቀድሞ ማዘጋጀት፣
·         በመድረኮች በሚገኝ ግብአት አስፈላጊ የሆኑ አደረጀጀቶችን ለመፍጠር የሚያስችል አቅጣጫ መቀየስ፣
·         ለዚህም የፌዴሬሸን ምክር ቤት ሚና ከፍተኛ መሆን አለበት፡

2        የመንግስታት የእርስ በእርስ ግንኙነት ምን ማለት ነው?
2.1    የመንግስታት ግንኙነት ምንነት (Definition)


በአጠቃላይ የመንግስታት ግንኙነት  የፌዴራል ስርዓት አንድ አካል ሲሆን በሁለት ወይንም ከዚያ በላይ በሆኑ ህግ የማውጣት፣ የመፈፀም፣ የመተርጎም እና የፋይናንስ ገቢ የመሰብሰብ ህገ-መንግስታዊ ስልጣን ባላቸው የመንግስታት እርከኖች ወይም በነዚህ አካላት ተቋማት መካከል በጋራ ወይም በጣምራ በተሰጣቸው እንዲሁም መደራረብ በሚታይባቸው ስልጣኖች ዙሪያ ፖሊሲዎቻቸውን፣ ፕሮግራሞቻቸውን፣ ስትራተጂዎቻቸውንና ዕቅዶቻቸውን ለማጣጣምና ለማቀናጀት እንዲሁም ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመፈጸም የሚያደርጉዋቸው የተዋረድና የጎንዮሽ መደበኛና መደበኛ ያልሆኑ ግንኙነቶች ናቸው፡፡

የተለያዩ ፀሐፊያን የመንግሥታት ግንኙነትን በተለያየ መንገድ ይተረጉሙታል፡፡ ለምሳሌ ያህል መንግሥታት ከሚጠቀሙበት ትርጉም የተወሰኑትን ከዚህ በታች አቅርበናቸዋል፡፡

የደቡብ አፍሪካ ሕገ-መንግስትን ተከትለው የወጡ ሕጎች ስናይ የመንግሥታት ግንኙነት በሶስት የመንግሥት እርከኖችን ማለትም በብሔራዊ፣ ክልላዊና አካባቢያዊ መንግሥታት መካከል ያለውን ውስብስብና መረዳዳትን የሚሻ ግንኙነትን እንዲሁም በእነዚህ አካላት መካከል ያለውን የፖሊሲ ትብብርን የሚያመላክት ትርጉም ተሰጥቶት እናገኛለን፡፡
IGR refers to the complex and interdependent relations amongst three spheres of governments as well as the coordination of public policies amongst the national, provincial and local government (DPLG, Inaugural Report, South Africa, 2005/06-2006/07).
በተመሳሳይ መልኩ በአውስትራሊያ የመንግሥታት ግንኙነት እንደሚከተለው ተገልፆአል፡፡
የመንግሥታት ግንኙነት በፌዴራል ሥርዓት ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ መንግስታት በትብብር ላይ የተመሰረተ ፖሊሲ እንዲኖራቸው ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር የግንኙነት ሥርዓት ነው፡፡

‘Intergovernmental relations are the responses that have been developed to facilitate cooperative policy making among divided governments within a federal system’ (Appendix 1, Intergovernmental Relations in Federal System, 2006). 
‘IGR is the set of processes and relationships between elected members and officials which affect and effect service delivery and which can be generally taken to consist of communicating information,  consultation and engagement’ (ASALGP 2005). 
ይህም እንደ ደቡብ አፍሪካው ሁሉ በሁሉም የአስተዳደር እርከኖች ላይ ያለውን ግንኙነትና የፖሊሲ ትብብርን የሚያመላከት ነው፡፡

2.3 የመንግስታት ግንኙነት አስፈላጊነት

·                  የተቀናጀ አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓትን ያሰፍናል፣
የመንግስታት ግንኙነት አስፈላጊነት የሚመነጨው በፌዴራል ስርዓቱ የስልጣን ክፍፍል ውስጥ ካለው የስልጣን መደራረብ፣ መጋራትና መጣመር የተነሳ እንደሆነ ከላይ ተገልጿል፡፡ ለህብረተሰቡ የሚሰጥ አገልግሎት በፌዴራል፣ በክልልና በወረዳ የስልጣን እርከኖች ውስጥ ማለፉ ግድ ነው፡፡ መንግስታቱ በጋራ በተሰጧቸው ስልጣኖች ላይ ለተገልጋዩ ህብረተሰብ ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት መስጠት ካለባቸው በዚህ ዙሪያ የሚያወጧቸው ፖሊሲዎች፣ ፕሮግራሞችና ዕቅዶች እንዲሁም አፈፃፀማቸው የተጣጣመና የተቀናጀ መሆን አለበት፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ በመንግስታቱ መካከል ቋሚና መደበኛ የሆነ የግንኙነት ስርዓት ሊኖር ይገባል፡፡

·         በክልሎች የስልጣን ወሰን ሃገራዊ ዓላማን ለማሳካት ይረዳል፣

በክልሎችና ወረዳዎች የስልጣን ወሰን ሃገራዊ ዓላማንና ተመጣጣኝ የአገልግሎት አሰጣጥ ስታንዳርድን ለማረጋገጥ፣ ፌደራል አወቃቀር በተለያዩ የስልጣን ጉዳዮች ሃላፊነቶች ላይ የመንግስታት ትብብርን ይጠይቃል፡፡ ከመንግስታቱ የጋራና የራስ ጥቅሞች የሚመነጩ ዓላማዎች፣ ፕሮግራሞችና ዕቅዶች ተግባራዊ የሚያደርጉት በመተባበርና በመደጋገፍ ብቻ ነው፡፡ ይህንን በፍላጎት ላይ የተመሰረተ ትብብርና መደጋገፍ የሚያስተባብርና የሚያቀናጅ ተቋማዊ የግንኙነት ስርዓት እንዲኖር ማድረግ ለዓላማዎቻቸው ስኬት በጣም ተፈላጊ ነው፡
·         አለመግባባትና ግጭቶችን ለመፍታትና ለማስወገድ ያስችላል፣

በመንግስታቱ መካከል በብዙ ጉዳዮች ላይ አለመግባባቶችና አልፎ አልፎም ግጭቶች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ ስርዓቱ በባህሪው ዳይናሚክ በመሆኑ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የቴክኖሎጂ ለውጦች ፈጥነው ይታዩበታል፣ ከዚህ ጋር በተያያዘ የፍላጎቶች እድገትና ለውጦች ይከሰታሉ፡፡ እነዚህ የፍላጎት ለውጦች ሁሌም የጋራ ጥቅሞችን በሚያጎለብት መልኩ እንዲማሉና፣ ወይም የተናጠል ፍላጎቶች ቢያንስ የአንድ ወይም የተወሰኑ ወገኖችን ጥቅሞች ሳይጎዱ እንዲሳኩ ከተፈለገ በእነዚህ ወገኖች/መንግስታት መካከል መደማመጥ፣ መመካከር፣ መወያየት፣ አንዱ የሌላውን ይሁንታ መጠየቅና መተባበር የማይቀሩ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ይህንን የመሰለ ግንኙነት ውጤታማ የሚሆነው ስርዓት ባለው የመንግስታት ግንኙነት ሲመራ ነው፡፡ 
በፌዴራል ስርዓት ውስጥ የጋራና ጣምራ ስልጣኖቻቸውን በመተግበር ሂደት በመንግስታቱ መካከል የስልጣን ይገባኛል ጥያቄና አለመስማማት ሊከሰት ይችላል፡፡ በስልጣን ላይ ለሚነሱ አለመግባባቶችና ግጭቶች መነሻና አፈታት ዘዴ አስቀድሞ በማጤን በትብብር ለመሥራት ያስችላል፡፡ ከመወነጃጀል ይልቅ ተደጋግፎ የመስራት ተነሳሽነትን ለማዳበር፣ ተናቦና ተሳስቦ በመስራት በመንግስታት መካከል እንዲሁም በህዝቦች መካከል ወንድማዊነትን ለማጎልበት፣ መንግስታትና ህዝቦች አንድ ዓይነት ሀገራዊ ራዕይ እንዲኖራቸው ለማስቻል፣ አንዱ ስለሌላው እንዲገደው፣ እንዲረዳዳና እንዲቻቻል ለማድረግ እና በአጠቃላይ በአንድ ሃገር ውስጥ በብዙህነት ውስጥ ያለውን አንድነት ለማጠናከር ያለመ ነው፡፡
በመንግስታቱ መካከል የስራ ድግግሞሽ በማስቀረት የሃብት ብክነትን ይቀንሳል፣ ውጤታማነትና ቅልጥፍና ይጨምራል፡፡
3          የመንግሥታት እርስ በእርስ ግንኙት ሂደቶች
የመንግስታት ግንኙነት አጠቃላይ ዓላማ ስንመለከት በፌዴራል ስርዓት ውስጥ ያሉ መንግስታት የጋራ ጥቅሞቻቸውን የሚያስጠብቁበት እንዲሁም ፖሊሲዎቻቸውን፣ ስትራተጂዎቻቸውን፣ ፕሮግራሞቻቸውንና ዕቅዶቻቸውን የሚያስተሳስሩበት ስርዓት ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ በአንድ በኩል የተቀናጀና ወጥ የሆነ አሰራርን ለማስፈን በሌላ በኩል ብዙህነትንና ፈጠራን (Innovation in Diversity) ለማበረታታት በሚደረገው ጥረት ላይ ሚዛን መጠበቅን ዓላማ ያደረገ መሆን አለበት፡፡ (Watts, 2006) ስለሆነም ግንኙነቱ የሚከተሉትን ዝርዝር ዓላማዎች ይኖሩታል፡-

o   መንግስታቱ በጋራ በተሰጣቸው ስልጣን ላይ የሚያስማሙና የተናጠል ፍላጎታቸውን የሚያቀራርቡ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች፣ ፕሮግራሞችና ዕቅዶች አንዲያወጡና የተቀናጀ አፈፃፀም እንዲኖራቸው ለማድረግ፣
o   በክልሎችና ወረዳዎች የስልጣን ወሰን ሃገራዊ ዓላማን ለማሳካት፣
o   በመንግስት እርከኖች መካከል ለሚነሱ አለመግባባቶችና ግጭቶች መነሻና የአፈታት ዘዴ አስቀድሞ በማጤን በትብብር ለመስራት፣
o   ከመወነጃጀል ይልቅ ተደጋግፎ የመስራት ተነሳሽነትን ለማዳበር፣ ተናቦና ተሳስቦ በመስራት በህዝቦች መካከል ወንድማዊነትን ለማጎልበት፣
o    መንግስታት ወይም ህዝቦች አንድ ዓይነት ሃገራዊ ራዕይ እንዲኖራቸው ለማስቻል፣
o   አንዱ ስለ ሌላው እንዲገደው፣ እንዲረዳዳና እንዲቻቻል ለማድረግ እና በአጠቃላይ በአንድ ሃገር ውስጥ በልዩነት ውስጥ ያለውን አንድነት ለማጠናከር፣
o   ጥራትና ውጤታማ የፖሊሲ፣ ስትራተጂና ዕቅድ አፈፃፀም ልምዶችን ለመለዋወጥ፣
o   የስራ ድግግሞሽን በማስቀረት ብክነትን ለማስወገድና የአፈፃፀም ቅልጥፍናን ለመጨመር፣
o   በፌዴራል፣ በክልልና በወረዳ መንግስታት መካከል የመረጃ ልውውጥን ለማፋጠንና የመረጃ አተናተን ጥራትን በማሻሻል ለተሻለ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ድጋፍ ለማድረግ የሚሉ ዓላማዎችን ያካትታል፡፡

3.1. የግንኙነቱ ገጽታና ስፋት
የመንግስታት ግንኙነት ሁለት ዓይነት ገጽታዎች (Dimensions) አሉት፡፡ አንደኛው የተዋረድ (Vertical) ግንኙነት ሲሆን በፌዴራልና በክልል፣ በክልልና ወረዳ ወይም በፌዴራልና ወረዳ መንግስታት መካከል የሚደረግ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በክልል ወይም በወረዳ መንግስታት መካከል የሚደረግ የጎንዮሽ (Horizontal) የግንኙነት ሥርዓት ነው፡፡
በሁለቱም የግንኙነት ገጽታዎች ላይ አንዳንድ ጊዜ ፌደራል  ከሁሉም ክልሎች እና/ወይም ወረዳዎች በሌላ ጊዜ ደግሞ ፌደራል ከተወሰኑ ክልሎች እና/ወይም ወረዳዎች ጋር በግንኙነት ላይ የሚሳተፍበት፤ ወይም በተወሰኑ ክልሎች እንዲሁም በተወሰኑ መስተዳድሮች መካከል የሚደረግ ግንኙነት ሊሆን ይችላል፡፡ የግንኙነቱ መስክ ወይም ፍሬ ጉዳይ የፌደራል መንግስትና የሁሉንም ክልሎች/ወረዳዎች የስልጣን ወሰን ወይም ፍላጎት (Interest) የሚነካ ከሆነ ግንኙነቱ ሁሉንም ክልሎች ያሳትፋል፡፡ ነገር ግን ግንኙነቱ በተወሰኑ ክልሎች/ወረዳዎች ስልጣንና ፍላጎት ላይ የሚያጠነጥን ከሆነ የሁሉም ክልሎች/ወረዳዎች ተሳትፎ አላስፈላጊ ስለማይሆን የተወሰኑት ብቻ የሚሳተፉበት ይሆናል፡፡
በፌዴራልና በክልሎች መካከል ያለው ግንኙነት በፖለቲካ መሪዎች ደረጃ በተለይ በፖሊሲ ላይ ትኩረት በመስጠት የሚካሄድ ግንኙነት ወይም በፌዴራልና ክልል ሴክተር ቢሮዎች መካከል በተግባራዊ እንቅስቃሴ ደረጃ (Functional Level) የሚደረግ ግንኙነት ሊሆን ይችላል፡፡ ክልሎች ድግግሞሽን ለማስቀረት፣ ግጭቶችን በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት፣ የጋራ የልማት ፕሮጀክቶችን በተቀናጀ መንገድ ለመተግበር ወ.ዘ.ተ… የእርስ በእርስ የግንኙነት መድረክ ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡

በአጭሩ በፌደራል ስርዓት ብዙ ስልጣንና ሃላፊነቶች የተወሳሰቡና የተደራረቡ ስለሆኑ ፌዴራል አገሮች ሁለቱንም ዓይነት ግንኙነቶችን መስርተው እየተጠቀሙባቸው ይገኛሉ፡፡
3.2. የግንኙነቱን ሁኔታ የሚወስኑ ጉዳዮች (Determinant Factors of IGR)

ፌዴራል አገሮች የመንግስታት ግንኙነት ምስረታ ታሪካቸው የተለያየ ነው፡፡ አንዳንዶቹ (ለምሳሌ ደቡብ አፍሪካ) ከጅምሩ የመንግስታት ግንኙነት የፖሊሲ አቅጣጫና የአፈፃፀም ማዕቀፉ በፌደራሉ ሕገ-መንግስት እንዲደነገግ ያደርጋሉ፡፡ ሌሎች (ለምሳሌ ካናዳ) ደግሞ በአፈፃፀም ሂደት በሚያጋጥም መነካካትና መደራረብ ምክንያት የተለያዩ ግንኙነቶችን ለመመስረት ይስማማሉ፡፡ ይህንን የተለያየ የመንግስታት ግንኙነት ታሪካዊ ሂደት እንዲኖራቸው የሚያደርጉ፣ የግንኙነቱን መልክና ጥልቀት የሚወስኑ የተለያዩ ምክንያቶች ይዘረዘራሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ የተወሰኑ ምክንያቶች (Factors) የሚከተሉት ናቸው፡፡

1)     ህገ-መንግስታዊ የስልጣን ክፍፍል፡- የመንግስታት ግንኙነትን ዓይነትና ስፋት እንዲሁም ቀድሞ ወይም ዘግይቶ እንዲጀመር የሚወስኑ ጉዳዮች፤ ለመንግስታቱ የተከፋፈለ ስልጣን ዝርዝርነትና ግልጽነት፣ የስልጣን መደራረብ መጠን፣ የጋራ ስልጣን ስፋት፣ ክልሎች የራሳቸውን አንፃራዊ ነፃ ስልጣናቸውን የሚከውኑበት የማዕቀፍ ስልጣን መኖር አለመኖር፣ ህግ የማውጣትና የማስፈፀም ስልጣን፤ ውክልና የመስጠት ድንጋጌ መኖር አለመኖሩ፣ የፌዴራል ስልጣን ልዕልናን (Federal Supremacy) የሚገልጽ ድንጋጌ መኖር አለመኖሩ፣ የአደጋ ጊዜ አዋጅ ድንጋጌ መኖር አለመኖሩ እና የቀሪ ስልጣን (Residual Power) ስፋት ወ.ዘ.ተ…ናቸው፡፡
2)     አወቃቀር፡- በእያንዳንዱ የመንግስት እርከን ውስጥ ያለው የህግ አውጪና አስፈፃሚ አካላት አወቃቀርና ግንኙነት፣ የመንግስት አወቃቀሩ ፓርላመንታዊ ወይም ፕሬዚደንታዊ መሆኑ፣ የህግ አውጪና አስፈፃሚ አካላት ስልጣን መለያየት፣ የፌዴራል ስርዓቱ ዓይነት (Dual & Executive Federalism) የመንግስታት ግንኙነትን ዓይነትና ጥልቀት ይወስናሉ፣
3)    ሕገ-መንግስታዊ ድንጋጌ፡- ህገ-መንግስቱ ስለ መንግስታት ግንኙነት መዋቅሮችና ፕሮሲጀራል ሂደቶች ያስቀመጠው ድንጋጌ፣
4)    የፌዴራል ሁለተኛ ምክር ቤት አወቃቀርና ሚና፡-  ላዕላይ ምክር ቤቱ የክልል መንግስታትን ተወካዮች ያካተተ ፎረም በመሆን ያገለግላልን? የትኛውን የመንግስት አካል (ህግ አውጪውን፣ ህግ አስፈፃሚውን) ወይስ መራጭ ህዝቡን ይወክላል? ህግ የማውጣትስ ስልጣን አለውን?
5)     የፖለቲካ ፓርቲዎች ርዕዮተ ዓለማዊ መመሪያና ግንኙነት፡- በስርዓቱ በተለይም በተለያዩ መንግስታት ውስጥ ያሉ ፓርቲዎች ግንኙነት፣ በተለያዩ የመንግስት መስተዳድር ውስጥ የተለያዩ ፓርቲዎች መኖር አለመኖራቸው፣ የፓርቲዎቹ የርዕዮተ ዓለም ልዩነቶች፣ የፓረቲ ቻናሉ ሚና በግንኙነቶች፣ ፓርቲ ቻናሉ ክልላዊ ፍላጎትን የማንፀባረቁ ሁኔታ፣
6)     የፍትህ አካሉ ሚና፡- በመንግስታቱ መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችና መሳሳቦች በህግ ተርጓሚው የሚፈቱበት ሁኔታና መጠን፣
7)     የክልሎች የፋይናንስ ሁኔታ፡- ክልሎች ምን ያህል ሃላፊነታቸውን ለመወጣት የሚያስችላቸው የራሳቸው የፋይናነስ ገቢ አላቸው? ወይም በፌዴራል መንግስቱ ድጎማ ላይ ያላቸው ጥገኝነት፣ በመካከላቸው ያለው የፋይናንስ አቅም ልዩነት፣ የፌደራል ድጎማን ለመሻማት የሚደረግ ሩጫና በቀመር ማከፋፈያው ላይ የሚታዩ ስምምነቶችና ልዩነቶች፣
3.3. ግንኙነቶቹ የሚካሄዱባቸው መንገዶች (Channels)

3.3.1 የአስፈፃሚ አካላት ግንኙነት
Ø  መረጃ ለመጋራት፣ የጋራ ችግሮች ላይ ለመወያየትና የጋራ እርምጃዎችን ለመውሰድ በየወቅቱ የሚደረጉ መደበኛና ኢ-መደበኛ ጉባኤዎችና ኮንፈረንሶች፣
    • የፌዴራል ጠ/ሚኒስትርና የክልል ፕሬዚዳንቶች የሚያካሂዱት ጉባኤዎች፣
    • ሴክተራል አስፈፃሚ መ/ቤቶች የሚያካሂዱት ስብሰባዎች፣
    • በሴክተር አስፈፃሚ መ/ቤቶች ያሉ ሲቪል ባለሙያዎች የሚያደርጓቸው ስብሰባዎች፣
Ø  መደበኛና ኢ-መደበኛ መንግስታዊ ስምምነቶችና ፕሮግራሞች፣
    • አስተዳደራዊ ዝግጅቶችና ስምምነቶች፣
    • የማስፈፀምና ማስተዳደር ስልጣኖች ውክልና፣
Ø  በሴክተር አስፈፃሚ መ/ቤት ሃላፊዎችና ባለሙያዎች መካከል የሚደረግ የዕለት ተዕለት የስልክ፣ ቴሌግራፍ …ወ.ዘ.ተ ግንኙነት - እነዚህ ኢ-መደበኛ የሆኑ ግንኙነቶች የትብብር መንፈስን ከመገንባት አንፃር በጣም አስፈላጊ ናቸው፡

 3.3.2 የህግ አውጪ አካላት ግንኙነት

Ø  ህግ የማውጣት ስልጣንን ከመተግበር በፊት ሌላኛውን የስልጣን እርከን ማማከር የሚጠይቅ ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌ -
Ø  ህግ የማውጣት ስልጣንን ከመጠቀም በፊት የሌላኛውን የስልጣን እርከን ይሁንታ ማግኘትን የሚጠይቅ ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌ -
Ø  ህግ የማውጣት ስልጣንን ከመጠቀም በፊት የፌዴራል ሁለተኛ ምክር ቤትን ይሁንታ ማግኘትን የሚጠይቅ ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌ፤በፌዴራልና ክልል መንግስታትን የሚወጡ ህጎችን ለማጣጣም፣

3.3.3  የፋይናንስ ግንኙነት
Ø  የበጀት ዝግጅት ከመጠናቀቁ በፊት የመንግስታቱን ምክክር የሚጠይቅ ፕሮሲጀር፣
Ø  በሁሉም የመንግስት እርከኖች ያለውን የበጀት ዝግጅትና አፈፃፀም ሂደት ማዕቀፍ የሚያሳይ የፌዴራል ድንጋጌ፣
Ø  ከፌዴራል መንግስት ለክልሎች የሚደረገውን የፋይናንስ ዝውውርን በተመለከተ የተቀመጠ ህጋዊ መመሪያ፣
Ø  የመንግስታዊ ፋይናንስ ዝውውር ጉዳዮችን በተመለከተ ሃሳቦችና ማስተካከያዎችን የሚሰጥ ነፃ ሆኖ የተመሰረተ የፋይናንስ ኮሚሽን ወይም በይነ-መንግታዊ ካውንስል፣

3.3.4     የመንግስታት ግንኙነት ድንጋጌ ዓይነቶች (Forms of Provision for IGR)
ሶስት ዓይነት የመንግስታት ግንኙነት ድንጋጌ አሉ፣ እነሱም የሚከተሉት ናቸው፡፡
1. ህገ - መንግስታዊ ድንጋጌ
§  የግንኙነቱን ሁኔታ ለመመስረት፡- በሕገ-መንግስቱ ለእያንዳንዱ መንግስት የተሰጡ ስልጣኖች እና በእያንዳንዱ የመንግስት እርከን የህግ ማውጣትና ማስፈጸም ስልጣኖችን ግንኙነት በማሳየት፣
§  በሁለቱ የመንግስት እርከኖች መካከል ያለውን የግንኙነት መዋቅሮችና ፕሮሲጀሮችን በመዘርዘር፡- የፌዴራል ስልጣን ልዕልና ድንጋጌ፣ የይሁንታ/ስምምነት እና የምክክር ግዴታን የሚያስቀምጥ፣ የመንግስታት ግንኙነት ካውንስል መመስረትን፣ የአማካሪ ኮሚሽን መመስረትን እንዲሁም የሁለተኛ ምክር ቤት ቅርፅን የሚያሳዩ ድንጋጌዎች፣

2. ህጋዊ ድንጋጌ
ለጋራ ፕሮግራሞች የወጡ ድንጋጌዎች፣ መደበኛ በሆነ የመንግስታት ስምምነቶች የሚመሰረቱ መዋቅሮች ወይም ፕሮሲጀሮች፤
3. በልምድ/በተሞክሮ የዳበረ ወይም ብዙም መደበኛ ባልሆነ ስምምነት 
በቀላሉ ሊመሰረት የሚችልና ግትር ባለመሆኑ በበርካታ ፌዴራላዊና ያልተማከለ አስተዳደርን
የሚከተሉ ሃገራት በብዛት የሚዘወተር ነው፡፡
4 የመንግሥታት የእርስ በእርስ ግንኙት በኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት

4.1 ሕገ-መንግስታዊ መነሻዎች

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲ ሪፖብሊክ ሕገ መንግስት በቀጥታና በተዘዋዋሪ የመንግስታት ግንኙነትን የሚጠይቁ በርካታ ድንጋጌዎች አካቷል፡፡ የሕገ-መንግስቱ መግቢያ እንደሚያመለክተው የኢትዮጵያ ፌዴራል ስርዓት የተመሰረተው በብሄር-ብሄረሰቦችና ህዝቦች ነፃ ፍላጎትና መልካም ፈቃድ ነው፡፡ ዓንቀፅ 8(1) ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት መሆናቸውን ይደነግጋል፡፡ እነዚህ ማንነቶች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን ሙሉ መብት በአንቀጽ39 አጎናፅፎአቸዋል፡፡ ፌዴራልና ክልል መንግስታት ሕግ የማውጣት፣ ሕግ የመፈፀምና ሕግን የመተርጎም ስልጣን እንዳላቸው በአንቀፅ 50፣ 51 እና 52 ላይ ተደንግገዋል፡፡ እንዲሁም በበአንቀጽ 47(4) ሁሉም ክልሎች እኩል ስልጣን እንዳላቸው ተሰምሮበታል፡፡
የፌዴራል መንግስት የሃገሪቱን አጠቃላይ የኢኮኖሚ፣ የማሕበራዊና የልማት ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጅዎችና ስታንዳርዶችን የማውጣት ስልጣን እንዳለው በአንቀጽ51 የተገለፀ ሲሆን ክልሎች በስልጣን ወሰናቸው ላይ የኢኮኖሚ፣ የማሕበራዊና የልማት ፖሊሲዎች ስትራቴጁያዊና ዕቅዶች የማውጣትና የማስፈፀም ስልጣን ተስጥቶአቸዋል፣ ገቢን በተመለከተ የፌዴራል መንግስት የገቢ ስልጣን በ/96፣ የክልሎች የገቢ ስልጣን በአንቀጽ97 የጋራ የገቢ ስልጣን በዓ/98 እንዲሁም ተለይተው ስላልተሰጡ የታክስ/ገቢ ስልጣኖች በአንቀጽ 99 በዝርዝር ተቀምጠዋል፡፡ እነዚህና ሌሎች ዓንቀፆች በመንግስታቱ መካከል መደማመጥ፣ ውይይት ድርድር፣ መተባበር፣ መደጋገፍ አንዲኖር የሚያመለክቱና የማያስገድዱ ናቸው፡፡
‘በኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ጉዳዮች’ የሚለው የፌደራል መንግስት የፖሊሲና የስትራተጂ ሰነድ የጋራ የፖለቲካ ማህበረሰብን ስለመገንባት በሚያተኩረው ርዕሰ-ጉዳይ ላይ በፌዴራል መንግስትና በክልል መንግስታት መካከል ሊኖር ስለሚገባው ትብብርና ቅንጅት በዝርዝር ይተነትናል፡፡ ይህ ማለት የመንግስታት ግንኙነት አንድ የጋራ ማህበረሰብን ለመገንባት ያለው ሚና የሚያሳይ ነው፡፡
በኢትዮጵያ የደርግ መንግስት ከወደቀ ከ1983 ዓ.ም ወዲህ ጠንካራ የፌዴራል የመንግስት ስርዓት ተመስርቶ በተግባር ላይ መዋል ከጀመረ ከ15 ዓመታት በላይ ተቆጥሯል፡፡ ይህ የፌዴራል ስርዓት ዋነኛ ዓላማው በሀገሪቷ ብዙህነትን ማለትም የተለያዩ ብሔር ብሔረሰበቦችና ህዝቦች መብትና ፍላጎትን ጠብቆ አንድ የጋራ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ መፍጠር ነው፡፡
ይህ ፌዴራላዊ ስርዓት በሃገሪቷ የነበሩትን በርካታ ችግሮች ከመፍታቱ ባሻገር ለሃገሪቷ ብሔር ብሔረሰበቦችና ህዝቦች የሲቪል፣ ፖለቲካዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶችን አጎናጽፏል፡፡   ይህ ማለት ግን ከፌዴራል ስርዓቱ ሊገኙ የሚችሉ ጥቅሞች በሙሉ ተገኝተዋል ማለት አይደለም፡፡ የፌዴራል ስርዓቱ ከዚህ በላይ ጥቅም ሊሰጥ በሚችል መልኩ ማጎልበት ይቻላል፡፡ ለዚህም የስርዓቱ አዲስ መሆንና ለስርዓቱ አስፈላጊ የሆኑ ተቋማዊ አደረጃጀት አለመሟላት በምክንያትነት ሊጠቀሱ ከሚችሉ ምክንያቶች አንዱ ነው፡፡
አጠቃላይ፡-  በኢትዮጵያ ከመንግስታት የፋይናንስ ግንኙነትና ከመንግስታት የግጭት አፈታት ግንኙነት በስተቀር የመንግስታት ግንኙነት በምን መልኩ መመራት እንዳለበት የሚገልጽ ዘርዝር ያለ ድንጋጌ የለም፡፡
ነገር ግን በተዘዋዋሪም ቢሆን አስፈላጊነቱን የሚያመለክቱ ዓንቀፆች አሉ፡-
o      የፌዴራል መንግስትና የክልሎች ስልጣን በህገ-መንግስት ተወስኗል፡፡ ለፌዴራሉ መንግስት የተሰጠው ስልጣን በክልሎች መከበር አለበት፡፡ ለክልሎች የተሰጠው ስልጣን በፌዴራሉ መንግስት መከበር አለበት - አንቀጽ 50/8
o      የክልሎችን ወሰን በሚመለከት ጥያቄ የተነሳ እንደሆነ ጉዳዩ በሚመለከታቸው ክልሎች ስምምነት ይፈፀማል፡፡ የሚመለከታቸው ክልሎች መስማማት ካልቻሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የህዝቡን አሰፋፈርና ፍላጎት መሰረት በማድረግ ይወስናል - አንቀጽ 48/1
o      የፌዴራል መንግስት ለክልሎች የተመጣጠነ እድገት እንቅፋት ካልሆነ በስተቀር ለአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ፣ ለመልሶ ማቋቋምና ለልማት ማስፋፊያ ለክልሎች ብድርም ሆነ እርዳታ ሊሰጥ ይችላል፡፡ የፌዴራሉ መንግስት ክልሎች ለሚያስፈልጋቸው ወጪዎች የሚያደርገውን ድጎማ በሚመለከት ኦዲትና ቁጥጥር ያደርጋል - አንቀጽ 94/2
የህገ መንግስቱ መግቢያ፡- የሃገሪቷ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የጋራ ጥቅማቸውን ለማሳደግና ዘላቂ ልማትና ዲሞክራሲን ለማረጋገጥ የሚያስችል አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመመስረት ቃል መግባታቸውን ያሳያል፡፡

የማዕቀፍ ስልጣን፡-
o      የፌዴራል መንግስት የሀገሪቱን አጠቃላይ የኢኮኖሚ፣ የማኀበራዊና የልማት ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ዕቅድ ያወጣል፤ ያስፈጽማል (አንቀጽ 51 ቁ. 2)
o      የጤና፣ የትምህርት፣ የባሕልና ታሪካዊ ቅርስ፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሀገር አቀፍ መመዘኛዎችንና መሠረታዊ የፖሊሲ መለኪያዎችን ያወጣል፣ ያስፈጽማል (በአንቀጽ51ቁ.3)
o      የክልል መንግስታት የክልሉን የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የልማት ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ዕቅድ ያወጣሉ፤ ያስፈጽማሉ ይላል (አንቀጽ 52 ቁ.2 -ሐ)   
o      አንቀጽ 98- የፌዴራልና ክልል መንግስታት በጋራ የሚጥሉትና የሚሰበስቡት የጋራ የገቢ ምንጮች፣
o      አንቀጽ 50 ቁ.9- የፌዴራል መንግስት አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው በህገ-መንግስቱ ዓ/51 ከተሰጡት ስልጣንና ተግባራት መካከል ለክልሎች በውክልና ይሰጣል፣ አስፈላጊውን ወጪም ይሸፍናል፤
o      አንቀጽ 48 ቁ.1- በክልል መንግስታት መካከል ስለአከላለል የሚከሰቱ አለመግባባቶችና ግጭቶች አፈታት፣
o      አንቀጽ 94 ቁ.2- የፌዴራል መንግስት ለአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ፣ ለመልሶ ማቋቋምና ለልማት ማስፋፊያ ለክልሎች ብድርም ሆነ እርዳታ ይሰጣል፤
o      በህገ-መንግስቱና በፌዴራል አዋጅ የተዘረዘሩት ሌሎች  ህጎች…

 4.2 የግንኙነቱ ተጨባጭ ሁኔታ
በሃገራችን በተጨባጭ በርካታ መደበኛና መደበኛ ያልሆኑ ግንኙነቶች ይካሄዳሉ፤
የተዋረድ  ግንኙነቶች፡- በሴክተር መስሪያ ቤቶች መካከል፣
Ø   ትምህርት፣ ጤና፣ ፋይናንስና ገቢዎች፣ አቃቤያነ ህግ፣ ፒስካፕ ዘርፎች…
Ø   ምክር ቤቶች /የፌዴራልና የክልል ም/ቤቶች የጋራ መድረክ/
በጎንዮሽ ፡-  በክልሎች መካከል
Ø   የምስራቅ ኢትዮጵያ አምስቱ ተጎራባች ክልሎች ግንኙነት፣
Ø   የኦሮሚያና የሶማሌ ክልል የጋራ የትብብር መድረክ፣
Ø   የዓፋር ክልልና የትግራይ ክልል የትብብር መድረክ፤
Ø   የዓፋር ክልልና የአማራ ክልል የትብብር መድረክ፣
Ø   የአማራ ክልልና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የጋራ ትብብር መድረክ፣
Ø   የደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክልል እና የጋምቤላ ክልል የጋራ መድረክ፣  
የግንኙነቱ  ትኩረት
በመንግስታቱ መካከል የሚደረገው ግንኙነት የሚያተኩረው፡-
v   ሃገራዊ ስታንዳርዶችን ተግባራዊ ከማድረግ ጋር በተያያዘ፣
v   የሙያ፣ ቁሳቁስና ዓቅም ግንባታ ድጋፎችን በማድረግ ረገድ፣
v   ሃገራዊ ዕቅዶችን ከክልል ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ከማዛመድና ከማስተሳሰር አንፃር፣
v   የጋራ ፕሮግራሞችን በመቅረጽና በመተግበር ሂደት፣
v   መልካም ተሞክሮዎችና ልምዶችን በመለዋወጥ ላይ፣
v   የመረጃ ልውውጥ በማድረግ ላይ፣

ጉድለቶችና ተግዳሮቶች
v   በመንግስታት ግንኙነት ምንነትና መርሆዎች ላይ ያለው ግንዛቤ ማነስ፣
v   ግንኙነቱን የሚያስተባብርና የሚያጠናክር  ተቋማዊ አስራር ስርዓት አለመዘርጋት
v   ስብሰባዎችና ጉባኤዎች ወቅቱን ጠብቀው በአግባቡ አለመካሄዳቸው፣
v   በጋራ ዕቅድ ላይ ያለመመስረትና ያለመናበብ፣ የዕቅዶች አሳታፊ አለመሆን፣
v   የሚሰጡ ድጋፎች  ክፍተትና ፍላጎት መሰረት ያደረጉ አለመሆን፣
v   ስምምነት የተደረሰባቸውን የጋራ ፕሮግራሞችን በወቅቱ አለመተግበራቸው፣
v   ወቅታዊ የመረጃ ልውውጥ አለመኖሩ፣ተጠያቂነት ያለመኖር፣

5  የመንግስታት ግንኙነቶችን ተቋማዊ አደረጃጀት
የፌዴራል-ክልል እና የክልል- ለክልል ግንኙነት ተቋማዊ አደረጃጀት እንደየሀገራቱ ተጨባጭ ሁኔታ የሚለያይ በመሆኑ ምክንያት አንድ ወጥ የሆነ ተቋማዊ አደረጃጀት በሁሉም የፌዴራል ሥርዓት በሚከተሉ ሀገሮች ማግኘት ባይቻልም ሁሉም የፌዴራል ሥርዓት የሚከተሉ ሀገሮች በአንድ ወይም በሌላ መልኩ የሚገለጽ እና የሚተሳሰር የመንግስታት ግንኙነት አደረጃጀት አላቸው፡፡ በእኛ ሀገር ተሞክሮ ስናየው በአንዳንድ ክልሎችና ተቋማት መንግስታት ግንኙነት  ጅምሮች ከመኖራቸውም በላይ ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ ይህ በጎ ጅምር ልንመሰርተው  ላለው ሀገራዊ የመንግስታት ግንኙነት ሥርዓት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ከጅምሮቹ መካከል በየክልል መንግስታት የተመሰረቱ የልማትና ትብብር መድረክ ማስተባበሪያዎች እና ተጠሪዎች ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡
በፌዴራል መንግስትና በክልሎች፣ በክልሎች እና በክልሎች መካከል ስላሉ ግንኙነቶች  እንደአስፈላጊነቱም በክልሎች በራሳቸው የስልጣን ወሰን የሚደረጉ መደበኛ (Formal) የሆኑ የመንግስታት ግንኙነት ሂደቶች፣ የታዩ ጠንካራ ጐኖች፣ የታዩ ደካማ ጐኖች፣ በአሰራሩ ላይ መሻሻል ያለባቸው ጉዳዮችን ወ.ዘ.ተ… በሚገባ በመፈተሽ ምን አየነት ተቋማዊ አደረጀጀትና አሠራር ይኑር የሚለው ሊጠና ይገባል፡፡ የመንግስታት የእርስ በእርስ ግንኙነት በሁለት ወይም ከዚያ በላይ ባሉ አካላት መካከል በመደጋገፍ የሚደረግ ግንኙነት ቢሆንም ለህዝቦች ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ እድገት የራሱ አስተዋፅኦ ያለው በመሆኑ ግንኙነቱ እንዲጠናከር የሀገሪቱ ህግ አውጪ አካል በንቃት ሊከታተለው እና ሊደግፈው የሚገባ ከመሆኑም ባሻገር በግንኙነቱ ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን መፍትሔ ለመሻት አጋዥ ይሆናል፡፡
የፌዴራል-ክልል እና ክልል- ለክልል ግንኙነት ከፌዴራል ሥርአቱ እድገት አብሮ እያደገና እየጐለበተ የሚሄድ፤ የሚያጋጥሙትን የፖሊሲና የአሠራር ክፍተቶች ለመቅረፍ እንዲቻል ሂደቱን ከአለም አቀፍ ልምድ ጋር በመቀመር የጥናትና ምርምር ሥራዎችን እንዲከናወኑ ማድረግ፤ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር የፌዴራል ሥርአቱ እና ሕገ- መንግሥቱን መሠረት ያደረገ የመንግሥታት ግንኙነት ሂደት እንዲጐለብት ማድረግ ያስፈለጋል፡፡
ይህ ግንኙነት የሚጐለብተው ህብረተሰቡና አመራሩ ስለ ፌዴራል  አወቃቀር በተለይ ደግሞ የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝምን ልዩ ባህሪያት ላይ በቂ ግንዛቤ ሲኖረው ጭምር በመሆኑ ወደ ህብረተሰቡና አመራሩ ለማስረፅ ተከታታይነት ያለው የግንዛቤ መስጨበጫ እና የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ማካሄድ ያስፈልጋል፡፡ በሀገራችን ያለውን የፌዴራል ሥርዓት በማጠናከርና የመንግስታት ግንኙነቶች ሥራዎችን እውን በማድረግ ረገድ በጥናት የተደገፉ የተለያዩ የግንዛቤ ስጨበጫ ስልቶችን መቀየስ ያስፈልጋል፡፡ ስለፌዴራሊዝም እና መንግስታት ግንኙነቶች በየደረጃው በሚገኙ /ቤቶች ሥርዓተ-ትምህርት ውስጥ እንዲካተት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መሥራት ያስፈልጋል፡፡
በሀገራችን ፅንሰ ሃሳቡ አዲስ ከመሆኑ አንፃር ተከታታይነት ያላቸው ኮንፍረንሶችንና ወርክሾፖችን በማዘጋጀት ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ግንዛቤ እንዲኖራቸው የማድረግ ሥራ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ከላይ የተዘረዘሩት ተግባራት እንደተጠበቁ ሆኖ በመንግስታት ግንኙነቶች ዙሪያ በተግባር የታዩ ችግሮችን በመለየት በየደረጃው ላሉ የመንግስታት ግንኙነት ባለሙያዎችና ሌሎች ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት የሌሎች አገሮችን ልምድ በመቀመር ተከታታይነት ያለው ስልጠናዎችን መስጠት የዚሁ ስራ አካል ነው፡፡
 6 የመንግስታት ግንኙነቶችን ለማጠናከር የሚያግዙ ተሞክሮዎቻችን
የመንግሥታት ግንኙነት ወይም IGR የተዋረድና (Vertical) የጐንዮሽ (horizontal) የሆነ የግንኙነት ሂደቶችን የሚያካትት ሥርዓት ነው፡፡ በተዋረድ (Vertical) ግንኙነት - በፌዴራል መንግስት እና በክልል መንግስታት መካከል የሚደረግ የግንኙነት ሥርዓት ሲሆን፤ የጐንዮሽ (Horizontal) ግንኙነት - ደግሞ በክልል መንግስታት መካከል የሚደረግ የግንኙነት ሥርዓት ነው፡፡ በሁለቱም የግንኙነት ሂደት በሀገራችን ፌዴራሊዝም ሥርዓት የተከናወኑትን ጅምር ተሞክሮዎች መጥቀስ ይቻላል፡፡
በሀገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብቅ ብቅ እያሉ ያሉትን ተሞክሮዎች ስንመልከት፤የአፈ-ጉባዔዎች የጋራ መድረክ፣የትምህርት ባለሙያዎች የጋራ መድረክ፣ልዩ ድጋፍ ለሚሹ ክልሎች ድጋፍ የሚሰጥ የእገዛ ቦርድ፣ የፌዴሬሽን /ቤት በየክልሎቹ በመዘዋወር የሚያካሂደው የምክክር መድረክ፣የአቃቤያን ህግ የጋራ መድረክ፣ የዳኞች ጉባኤ፣ የፌዴራል መንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት  ከክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤቶች ጋር የሚያደርገው ግንኙነት፣ የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር ሚያካሂዳቸው መጠነ ሰፊ የአቅም ግንባታ ሥራዎች፣ የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ጋር በመተባበር  ከተመሳሳይ የክልሎች መ/ቤቶች ጋር የሚያደርገው ግንኙነት፤ የአምስቱ የምሥራቅ ኢትዮጵያ አጐራባች ክልሎች የጋራ መድረክ፣ የኦሮሚያና የሶማሌ ክልል የጋራ የትብብር መድረክ፣ የአፋርና የትግራይ፤ የአፋርና የአማራ ክልል የጋራ የትብብር መድረክ፣ የአማራና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የጋራ ትብብር መድረክ፣ የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል እና የጋምቤላ ሕዝቦች ክልል የጋራ ትብብር መድረክ፣ እንደ አብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ እነዚህ ግንኙነቶች የየራሳቸው የሆነ ሂደትና ደረጃ ላይ የሚገኙ ቢሆኑም ለጐንዮሸ ግንኙነት ሥርዓት ግንባታ የማይናቅ አስተዋጽኦ እያደረጉ በመሆናቸው የመንግሰታት ግንኙነትን በማጠናከር በኩል ጥሩ ተሞክሮዎቻችን ናቸው ማለት ይቻላል፡፡
የፌዴራል ክልል ግንኙነትን (IGR) የማስተባበርና የመምራት ሥልጣን ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር በአዋጅ ቁጥር471/1998 ከመሰጠቱ በፊት ክልሎችን የማስተባበር ስልጣን ተሰጥቶ የነበረው በጠቅላይ ሚኒስትር /ቤት ሥር ለነበረው የክልል ጉዳይ ዘርፍ ሲሆን፤ የዚህም ዘርፍ ሥራ በአብዛኛው ልዩ ድጋፍ በሚሹ ክልሎች ዙሪያ ያጠነጠነ ነበር፡፡ የባለቤትነትን ወይም የተጠሪነት ክፍተት የነበረውን የመንግስታት ግንኙነት ሥራ ወይም የፌዴራል ክልል ግንኙነት የማስተባበር ሥራ በአዋጅ ቁጥር 471/1998 .. በመሙላት ለፌዴራል ጉዳዮች / ተሰጥቷል፡፡ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 6 ላይ በተደነገገው መሠረት የፌዴራል ጉዳዮች / "በፌዴራል መንግስትና በክልሎች መካከል በመግባባትና በአጋርነት ላይ የተመሠረተ መልካም ግንኙነትና ትብብር እንዲኖር በማድረግ የፌዴራል ሥርዓቱ እንዲጠናከር የግንኙነት ማዕከል ሆኖ ያገለግላል " ስለሚል የመንግስታት ግንኙነቶችን የማጠናከር እና የፌዴራል ሥርዓቱ የግንኙነት ማዕከል ሆኖ የማገልለል ሚና በግንባር ቀደምትነት ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ይጠበቃል፡፡
ይኽ ሂደት የብዙ ባለድርሻ አካላትን ድጋፍና ትብብር የሚጠይቅ እና ከፌዴራሊዝም ሥርዓት ግንባታችን አንዱና አበይት ጉዳይ ስለሆነ በተለይ የፌዴራልና የክልል መንግስታት  አመራር  እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት  ሁለንተናዊ ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል፡፡
በአዋጅ ቁጥር 4/1987 አንቀጽ 1 እና በአዋጅ ቁጥር 471/1998 በግልጽ እንደተደነገገው እያንዳንዱ አስፈፃሚ ሚኒስቴር /ቤት በሚመለከተው የሥራ ዘርፍ የወጡትን ህጐች የማስፈፀም ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ እያንዳንዱ አስፈፃሚ አካል በህግ የተሰጡትን የማስፈፀም ስልጣን የሚተገብረው በፌዴራልናበክልሎች፤ በወረዳዎች እና በቀበሌዎች መሆኑ  የተለያዩ የመንግስት ሥልጣን እርከኖች ዉስጥ ማለፉ እና ትብብር መጠየቁ አይቀርም፡፡ እነዚህን የሥልጣን እርከኖች መስተጋብር ማረጋገጫው መንገድ የፌዴራል-ክልል እና የክልል- ለክልል  ግንኙነት ሥርዓት ነው፡፡ የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግስታት የየራሳቸው የሆነ ፖሊሲ ስትራቴጂና ዕቅድ የማውጣት ስልጣናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ  በፌዴራል መንግስት እና በክልል መንግስታት የሚወጡ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች መካከል መናበብ መኖር አለበት፡፡ ፌዴራል ደረጃ የሚወጣ ፖሊሲና ስትራቴጂ እንዲሁም ዕቅድ ተግባራዊ የሚሆነው በፌዴራል የሥልጣን ወሰን ሆኖ ከክልሎች የሥልጣን ወሰን ደረጃ ከሚወጡ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ጋር መናበብ ይኖርበታል፡፡ ክልሎችም ደረጃ የሚወጣ ፖሊሲና ስትራቴጂ እንዲሁም ዕቅድ ተግባራዊ የሚሆነው በየራሳቸው ክልል የስልጣን ወሰን ሆኖ በፌዴራል ደረጃ ከሚወጡ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ጋር መናበብ ይኖርበታል፡፡ በህገ-መንግስቱ የተቀመጠውን አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ መፍጠር የሚለው በዚህ ሁኔታ ከሚናበብ የመንግስታት ግንኙነት ሥርዓት (IGR) መሆኑ ይታመናል፡
በአንቀጽ 88 ቁጥር 2 ላይ መንግስታት የብሔሮችን፣ የብሔረሰቦችን እና የሕዝቦችን ማንነት የማክበርና በዚሁ ላይ በመመርኮዝ በመካከላቸው እኩልነት አንድነትና ወንድማማችነትን የማጠናከር ግዴታ እንዳለባቸው ይገለፃል፡፡ ሁለቱም መንግስታት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ወኪሎችና የእነርሱ ስልጣን መገለጫዎች ስለሆኑ በወከሉዋቸው ብሔረሰቦችና ህዝቦች መካከል አንድነትና ወንድማማችነትን የማጠናከር ግዴታቸውን መወጣት የሚችሉት መጀመሪያ በተወካዮቹ መካከል የሰመረ የግንኙነት ሥርዓት (IGR) ሲኖር ነው፡፡
7  የመንግስታትና የባለድርሻ ኣካላት ፍላጎት
በኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓቱ ከተመሰረተ ጀምሮ በመንግስታት (ፌዴራልና ክልል) መካከል ግንኙቶች የነበሩ ሲሆን በሂደት እየሰፉና እየጎለበቱ መጥተዋል፡፡ የፀጥታ አካላት የጋራ ፎሮሞችና የትብብር/የመደጋገፍ ዕቅዶች ነበሯቸው፡፡ በሂደት በፌደራል ሚ/ር መስሪያ ቤቶችና በአቻ ክልል ቢሮዎች የጋራ መድረኮች እየሰፉ መጡ፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ጀምሮ ደግሞ በፌዴራልና በክልሎች አፈ-ጉባኤዎች መካከል በምክክርና ልምድ ልውውጥ ላይ ያተኮረ ዓመታዊ ፎረም እየተካሄደ ሲሆን፤ የፌዴሬሽን ም/ቤት በፌዴራሊዝም ላይ ግንዛቤን የማስፋት መድረክ በየዓመቱ በክልሎች እየተዘዋወር በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
ከዚህ በተጨማሪና የመንግስታት ግንኙነት መርህ መሰረት ያደረገ ግንኙነት በ5ቱ የምስራቅ ኢትዮጵያ ተጎራባች ክልሎች መካከል ተጀምሯል፡፡ ይህ ግንኙነት የጋራ የትብብር ስምምነት ሰነድ በመፈራረም የተመሰረተ በመሆኑ ከሌሎቹ ግንኙነቶች የላቀ ያደርገዋል፡፡ ሌሎች ተጎራባች ክልሎችም የጋራ የትብብር ሰነድ ባይፈራረሙም ትብብርና መደጋገፍ ዓላማ ያደረጉ ግንኙነቶች አሉዋቸው፡፡ ይህ የሚያመለክተው ከፌዴራል ስርዓቱ ባህሪ የሚመነጩ የመንግስታት ግንኙነቶች እየተካሄዱ መሆናቸውን ብቻ ሳይሆን ለተመሳሳይ አፈፃፀምና ዘላቂ የጋራ ህልውና ተፈላጊ መሆኑ ሁሉም መንግስታት እየተገነዘቡ መምጣታቸውን ነው፡፡
ከዚህ አልፎ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የመንግስታት ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችል ተቋማዊ ስርዓት መገንባት እንደሚገባ እየጠቆሙ ይገኛሉ፡፡ የሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፌዴራል ጥናት ኢንስቲትዩት መምህራንና ባለሙያዎች እስከ አሁን እየተካሄዱ የሚገኙ የመንግስታት ፎሮሞችና ትብብሮች የመንግስታት ግንኙነት ተቋማዊ መርህና የአመራር ስርዓት በመከተል እንዲጎለብቱ የሚያስችሉ ሕጋዊ ማዕቀፎች፣ ስትራቴጅዎች፣ ኘሮሲጀሮች፣ አደረጃጀቶችና ፎሮሞች መቀረፅና መመስረት እንዳለባቸው ይገለፃሉ፡፡ ስለሆነም የመንግስታት ግንኙነት አስፈላጊነት እየጎላ መምጣቱን ያመለክታል፡፡
ለመንግስታት እርስ በእርስ ግንኙነት አደረጀጀት መፍጠር
IGR ወይም የመንግሥታት አርስ በእርስ ግንኙነት በፌዴራል ሥርዓቱ በተገቢው ሁኔታ ነገር ግን የፌዴራል ሥርዓቱ በተገቢው ሁኔታ እንዲጠናከርና ሥር እንዲሰድ እንዲሁም ሕገመንግስቱ ያስቀመጣቸው ሀገራዊ ግቦች እና ከሕገ-መንግስቱ የመነጩ ሕጐች፣ ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች በተገቢ መንገድ ሥራ ላይ እንዲውሉ ማስቻያ ዘዴ (means to an end) ነው፡፡
ስለዚህ IGR የማተገበረው የፌዴራሉን ሥርዓትና የሕገ-መንግሰት መርሆዎችን መሠረት ባደረገ መልኩ ሊሆን ይገባል፡፡ ከነዚህ መርሆዎች ውስጥ እንደ Separetion of Power በፌዴራል መነግስትና በክልሎች መካከል እንደሁም በመንግሥት አካላት መካከል /ሕግ አውጪ፣ ሕግ ተርጓሚ፣ ሕግ አስፈፃሚ/ መካከል ያለውን የሥልጣን ክፍፍል መሠረት ያደረገ መሆን አለበት፡፡
አደረጃጀቶቹ ሲፈጠሩ የመነግሰት አካላት መካከለ ያለውን የሥልጣን ክፍፍለ እና በተለይ እንደ ዳኝነት የሉ ነፃነትን በሚጐዳ መልኩ መፈጠር የለባቸውም፡፡
ሕገ -መነግሰቱ በተለይ ለአስፈፃማው የሀገሪቱን ኢኮኖሚየዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ዕድገት በማፋጠን አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚያስችል ስልጣን በፌዴራሉም ሆነ በክልል ሰጥቷል፡፡  እንዝህን ውጤታማ ለማድረግ IGR አይነተኛ መሣሪያ ነው፡፡
ለሕግ አውጪው እንደዚሁ ለኢኮኖማው፣ ለፖለቲካዊ ማህበራዊ ዕድገት እና አጠቃላይ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደርን ለማስፈን እንዲቻል ምቹና ማስቻያ ሕጐች፣ አስፈፃሚውን በመቆጣጠር ሀገሪቱ በሕገመንግሰቲ የተቀመጠውን የአንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማሕበረሰብ የመገንባት አላማን ከግብ እንድታደርስ ከፍተኛ ሀላፊነት አለበት፡፡ በተለይም ሕጐች (social engineering) የማህበራዊ ምህድሰና አካል በመሆናቸው በክልል ሆነ በፌዴራል ደረጃ የሚወጡ ሕጐች ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡
በዚሁ የመንግስት አካል ውስጥ የፌዴሬሸን ም/ቤት ሚና በጣም የጐላ ነው፡፡  ይኸውም
በመጀመሪያ ደረጃ ሕገ-መንግስቱን በመተርጐም በተሻለ መልኩ እንዲፈፀም በማድረግ በሀገሪቱ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ዕድገት ----ያለ ሚና መጫወት የሚያስችል ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡  ከዚህ በተጨማሪ ያለመግባባት በፎዴራል መንግስት እና በክልሎች መካከል እንዲሁም በክልልና ክልል መካከል ሲከሰት መፍተሔ የመስጠት ሥልጣን አለው፡፡ ይኸም በሀገሪቱ የፌዴራል ሥርዓት በተሻለ ሁኔታ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን እየፈታ፣ እየጐለበት የሚሄዱ ያደርገዋል፡፡  በሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 62 ሥራ የተዘረዘሩት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሥልጣንና ተግባርን ለማከናወን የ IGR መሣሪያነት ወሣኝ ነው፡፡
የዳኝነት አካሉ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 78 የተደራጀ በመሆኑ በተለይ በንዓስ አንቀፅ 78/2/ እና 3 ክልሎች በተጨማሪ የፌዴራሉን የመጀመሪያና የከፍተኛ ፍርድ ቤት ሥልጣን የተሰጣቸው በመሆኑ ይኸንን እና ሌሎች የዳኝነት ሥርዓቱን በተመለከተ ለሚያደርጐት ግንኙነት  IGR ወሣኝ መሣሪያ ነው፡፡
ከላይ ከተገለፀው ሀሳብ መነሻ ስንነሳ የፌዴራል ሥረዓታችን የትብበር እንደመሆኑ IGR
1.   በክልል እና በፌዴራል አስፈፃሚ መካከል
2.   በክልልና በፌዴራል ሕግ አውጪ መካከል
3.   በክልልና በፌዴራል ሕግ ተርጓሚ መካከል በተደራጀ መልኩ ሊኖር ይገባል

የአደረጃጀቶቹ ቅርፅ
1.  በአስፈፃሚው መካከል ዋነኛ የኢኮኖሚ የፖለቲካና የማህበራዊ ጉዳዮች በተለይ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ እንዲሁም የሕግ የበላይነት ጉዳዮች በዓመት ቢያንስ ሁለት ጊዜ የሚመከርበት ኮንፍረንስ ሊኖር ይገባል፡፡
2.  በሕግ አውጪው መካከለ ከዚህ ቀደም የነበረውን መድረከ በማጠናከር በተሻለ አደረጃጀት እንዲመራና ተቋማዊ አሠራር እንዲኖረው በማድረግ ማጠናከር ይቻላል፡፡
3.  የሕግ ትርጉም መድረክም እንዲሁ ተቋማዊ በሆነ መልኩ ሊደራጅ ይችላል፡፡
4.  አሁን ባለንበት የሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ከተሞች የተለየና ዘመናዊ አሠራር የሚፈልጉ በመሆናቸው ይኸንን መሠረት ያደረገ የ IGR ሥራ ያስፈልጋል፡፡  ይኸም በማህበር መልክ የሀገሪቱ ከተሞች ተደራጅተው አንዱ ከአንዱ የሚማማርበት መድረክ መፍጠር ይገባል፡፡  ከዚህ ቀደም በከተሞች ቀን የተጀመረበትን ተሞክሮ ተቋማዊ በሆነ መልኩ በተጨማሪ ማስኬድ ይቻላል፡፡

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የፌዴሬሽን ም/ቤት ሚና
የፌዴሬሽን ምከር ቤት የኢትዮጵያ በሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሚወከሉበት ም/ቤት ሲሆን፣ የራፐብሊኩ የሉዓላዊ  ሥልጣን ባለቶች ይሀንን ሥልጣናቸውን ተግባራዊ የሚያደርጉበት ም/ቤት ነው፡፡  ይህም የሕገ-መንግሥቱ የበላይ ጠባቂ እና አስጠባቂም ጭምር፡፡

ሕገ-መንግስቱና የፌዴራል ሥርዓቱ በትክክል ተግባራዊ መሆኑን፣ በፌዴራል ሥርዓቱ ውስጥ ያለመግባባት ሲፈጠር በሕገ-መንግስቱ መሠረት የመፍታት በራሱም የክልሎችና የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዘቦችን መብት በሚመለከት የሚመክርብት ተቋም በመሆኑ በተሰጡ የ IGR ሥራን የሚያከናውን ተቋም ነው፡፡  ከዚህ በተጨማሪ በአንቀፅ 62 እና በአዋጅ 251/1993 የተሰጠውን ሥልጣንና ተግባሪዊ ለማድረግ ም/ቤቱን ለዚህ ተልዕኮ በሚገባ ማዘጋጀት ተገቢ ነው፡፡

ይኸ እንዳለ ሆኖ ከላይ የጠቀስናቸው የIGR አደረጃጀቶች በሕገ-መንግስቱ የተደነገጉትን መርሆዎች ጠብቀው መደራጀታቸውን የመከታተል እና የማገዝ ሀላፊነት ጭምር የፌዴሬሸን ም/ቤት የሥራ ድርሻ ነው፡፡





1 comment:

  1. መልካም አስተዳደር ለማሳለጥ ጠቃሚ ጥናት ነወ፡፡

    ReplyDelete