ዩጎዝላቪያ እንዴት ፈረሰች?
=================
(በ ተበጀ ሞላ የተፃፈ)
ታሪክ መስታወት ነው፣ በራሳችን ዓውድ ላይ ቆመን የሌሎችን ዓውድ እንድንቃኝ ያስችለናል፡፡ ዛሬ ላይ ሆነን ትናንትን እንድናይ ይረዳናል፣ ጠቃሚ ትምህርት ይገኝበታል።
በአንደኛው የዓለም ጦርነት መጨረሻ የዩጎዝላቪያን ግዛት የመሠረቱ አድርያቲክ ባህር ዳርቻ የሚገኙ ስድስት ሪፐብሊኮችና ሁለት ራስ ገዝ ክልሎች፣ የሁለተኛው ዓለም ጦርነት እንዳበቃ የዩጎዝላቪያን ሶሻሊስት ፌዴራል ሪፐብሊክ ፈጠሩ።
ከአራት አሠርት ዓመታት የአብሮነት ቆይታ በኋላ፣ የጠንካራውን መሪ ጆሴፕ ቲቶን ሞት ተከትሎ፣ በቀዝቃዛው ጦርነት መጨረሻ ፌዴሬሽኑ ያልተጠበቀ አደጋ ገጠመው።
በ1980ዎቹ ሁለተኛ አጋማሽ የፈዴሬሽኑ አንድ አካል በነበረችው የሰርቢያ ክልል አክራሪ ኣሃዳዊያን ተነሱ። ከገዥው የኮሙዩኒስት ፓርቲ የተገኘ ስሎቦዳን ሜሎሰቪች የተባለ ትምክህተኛና ፅንፈኛ ሰርብ፣ ብሶት ተኮር ፖለቲካ ሠርቶ በርካታ ሰርቦች ወደ ቤልግሬድ አደባባይ እንዲወጡ አደረገ።
ቤልግሬድ የፌዴራሉ መንግሥቱ መቀመጫና የሰርቦች ዋና ከተማ ነበረች። በመሆኑም ሜሎሰቪች በፌዴራል መንግሥቱ የማያባራ ሕዝባዊ ጫና (Mob Pressure) በመፍጠር፣ እሱ ወደ ሥልጣን ካልወጣ መንግሥት ሰላም እንደማያገኝ አስታወቀ፣ ተሳካለትም። በወራት ውስጥ ለከፍተኛ ሥልጣን በቃ።
ችግሩ በዚህ አላበቃም። የሽንገላ ፖለቲካው ዘላቂ መፍትሔ አላመጣም። ሜሎሰቪች በሌሎች ክልሎች እየዞረ ለእሱ ፍላጎት ተገዥ የሆኑ አድርባዮችን ወደ ሥልጣን ማውጣት ጀመረ። በቮጅቮዲናና በሞንቴኔግሮ ግዛቶች ተሳካለት። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተጠቅሞ የብዙኃን አልባንያዎች መኖርያ በሆነችው ኮሶቮም የሰርቦችን የበላይነት አረጋገጠ። ሜሎሰቪች ‹‹በምድር ላይ አንዳችም ኃይል የሰርብን ሕዝብ ፍላጎት ሊገታ አይችልም›› በማለት በአደባባይ ደሰኮረ።
የሰርብ ፅንፈኛ ብትምክህተኞች ህልም ግን ብዙም ሳይርቅ ፈተና ገጠመው። በሰሜን ጫፍ ያለችው የስሎቫንያ ክልል በቀላሉ እጅ አልሰጠችም። የነገሮች አካሄድ አላምር ቢላቸው የዢዠክ አገር ሰዎች በቶሎ ከኮሙዩኒስት ፓርቲው ራሳቸውን አገለሉ። የሰሜን ምዕራቧ የክሮሽያ ክልልም እንዲሁ ለሰርብ ስግብግብ ኣክራሪ ትምክህተኞች አልንበረከክም አለች። ይህን ውጥረት ተከትሎ በመላው አገሪቱ በስፋት ተሠራጭተው ይኖሩ የነበሩ ሰርቦች ደኅንነታቸው አደጋ ላይ ወደቀ። ሜሎሰቪች ሁኔታውን እንደ መልካም አጋጣሚ ቆጠረው፡፡
ለሰርብ ፅንፈኛ ትምክተኞች ፍላጎት ያልተንበረከኩ ክልላዊ መንግሥታትን ለመምታት ሊጠቀምበት ወሰነ። የሜሎሰቪች ሰዎች የሰርብ ብሔር ተወላጆች በያሉበት እንዲደራጁና እንዲታጠቁ አደረጉ።
የብሔርተኞቹ እንቅስቃሴ በዚህ ብቻ አላቆመም። የፌዴራል መንግሥት ቁልፍ የሥልጣን ቦታዎችም በሰርቦች እጅ እንዲገቡ ተደረገ። እንደ ሞንቴኔግሮ የመሳሰሉ ክልሎችም የሰርቦች ጥቅመኞች ሆነው ለፅንፈኞቹ ያልተገደበ ድጋፍ ሰጪ ሆኑ። ሜሎሰቪች በተፈለገው ጊዜና ቦታ የሚታዘዝ የሰርብ ልዩ ኃይልም አደራጀ። የታሪክ ቁርሾ ጥሩ የጥፋት ግብዓት ሆኖ ተገኘ። የኮሶቮ አልባንያዎችና ክሮሺያውያን በተለያየ ዘመን በሰርቦች ላይ ፈጸሙት የተባለው በደል እንደ አዲስ በቴሌቪዥን መተረክ ጀመረ።
ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ የክሮሺያ ክልል ፖለቲከኞች ሕገወጥ መሣሪያ ሲገዙ የሚያሳይ የተቀነባበረ የውሸት የቪድዮ ምሥል በቴሌቪዥን ተለቀቀ። በሕግ ማስከበር ስም ክልሉን ለመምታት የሚደረግ ዝግጅት ነበር። በመቀጠል በፌዴራል መንግሥቱ ያላቸውን ቁልፍ ሥልጣን ተጠቅመው የሰርብ ፅንፈኛ ትምክህተኞች፣ ‹‹በየትኛውም ክልላዊ መንግሥት ሕገወጥ መሣሪያ የታጠቀ በአስቸኳይ እንዲፈታ›› የሚል አዋጅ አወጡ። አዋጁን በማያስፈጽሙ አካላት የማያወላውል ዕርምጃ እንደሚወስዱም አስጠነቀቁ። የተጀመረውን ለውጥ ለመቀልበስ ብሎም ዩጎዝላቪያን ለመበተን በሚንቀሳቀሱ ‹‹የነውጥ ኃይሎች›› ላይ የከፋ የከፋ ቅጣት እንደሚጣል አስጠነቀቁ።
የሌሎች ክልል መንግሥታትና ሕዝቦች ክስተቱን በሥጋትና በአንክሮ ይከታተሉ ነበር። የሰርቦች ብሔራዊ ጡዘት በክሮሽያ ተመጣጣኝ ኃይል ፈጠረ። የጦርነት ነጋሪቱ ያደናበራቸው ክሮአቶች አክራሪ ብሔርተኞችን ወደ ሥልጣን አወጡ፡፡ እ.ኤ.አ. ሰኔ 1991 ዓ.ም የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው በመወሰን ነፃ አገር ለመሆን ወሰኑ፡፡ ለሉዓላዊነታቸው እንደሚዋደቁ ቃል ገቡ።
ከሰርቢያ ጋር ድንበር የማያገናኛቸው ስሎቫንያዎች በቀላል ኪሳራ ከፌዴሬሽኑ መውጣት ቢችሉም፣ ሌሎቹ ክልሎች ግን ከፅንፈኛ ርምክህተኞቹ ጋር ደም አፋሳሽ ትግል ማድረግ ነበረባቸው።
ሰርቦች የመጀመርያውን ዘመቻ በክሮሽያ ላይ ከፈቱ። ሜሎሰቪች ‹‹ከሰርቢያ ውጪ የሚኖሩ ሰርቦች ህልውና ያሳስበኛል›› በሚል ሰበብ በክሮሽያ ላይ ይፋ ጦርነት አወጀ። በፌዴራል መንግሥቱ ስም የጦር ኃይሉን ተጠቅሞ ገና በሁለት እግሮቿ ያልቆመችውን ክሮሽያ ክፉኛ አቆሰላት። ጥቃቱ በሒደት ወደ ቦስኒያና ኮሶቮ ሰፍቶ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎች ሕይወታቸውን አጡ። በርካቶች ቄዬአቸውን ጥለው ተሰደዱ። ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፉ የመጡ መተኪያ የሌላቸው ታሪካዊ ቅርሶች በእሳት ነደዱ።
በዚህ ሁሉ መሀል ‹‹የወንድማማችነታችን መገለጫ ዩጎዝላቪያ በጥቂቶች ሴራ አይፈርስም›› የሚሉ ተስፋቸው የፀና ዜጎች ነበሩ። የአውሮፓ ኮሚሽንም አሸማጋይ ሆኖ ‹‹አብሮ መኖር ቢሳናችሁ መጠፋፋት የለባችሁም›› ብሎ ተማፀነ። ጥረታችው ግን ለውጥ አላመጣም።
በፌዴራል መንግሥቱ ሽፋን የራሳቸውን ራዕይና ፍላጎት በሌሎች ላይ ለመጫን የሞከሩ ሰርቦች ዕቅዳቸው አከሰራቸው፡፡ ህልማቸውም ቅዠት ሆኖ አገኙት። የብሄር ጡዘቱን መሸከም ያልቻለችው ዩጎዝላቪያም በአጭር ግዜ እንደ ኣገር ውስጥ ተበታትና ከዓለም ካርታ ተፋቀች።
ፕሬዚዳንት ጆሴፕ ቲቶ እ.ኤ.አ. በ1974 የብሔሮችና ብሔረሰቦች የመገንጠል መብት በሕገ መንግሥት እንዲረጋገጥ ሲያደርግ፣ አገሩ ዩጎዝላቪያ ከ17 ዓመታት በኋላ እንዲህ ወደ ብዙ ሃገራት እንደምትቀየር አልተጠራጠረም ነበር።
የሰርቢያ አክራሪ ትምክህተኞች ከውጭም ከውስጥም በደረሰባቸው የተባበረ የጦር ምት ተደቁሰው፣ ባሉበት ተወስነው ክልላቸውን አገር አድርገው ሊኖሩ ግድ ሆነባቸው። የመገነጣጠል ጦሱ ዘላቂና የከፋ ነው። ከ30 ዓመታት በኋላ ዛሬም የኮሶቮ አልባንያዎችና ሰርቦች ሰላም የላቸውም። ድህነትም ሥር ሰዷል።
ዩጎዝላቪያን ያፈረሳት ሁሉን ነገር የእኔ ብቻ፣ በሁሉም ጉዳይ እኔ ብቻ ያልኩት ይሁን የሚል አልጠግብ ባይ የሰርብ ትምክህት ነው።
በጥሞና ላስተዋለ የዛሬ 30 ዓመት በዩጎዝላቪያ የሆነውና አሁን በእኛ አገር እያቆጠቆጠ ያለው ይሉኝታ ቢስ ፅንፈኛ ኣሃዳዊነት መመሳሰሉን ማስተዋል ግድ ይላል።
ከወዲሁ በጥንቃቄ ካልታሰበበት በእኛም አገር ሜሎሰቪች በቅለዋል፣ በእኛም አገር ሰርቦች አሉ። የኢትዮጵያን ሉዑላዊነት አረጋግጦ፣ የብሄር ማንነትንና ጥቅም የሚያስጠብቅ የፖለቲካ ፍኖተ ካርታ ያስፈልገናል። ለዚህ ደግሞ መሸነጋገሉን ትተን በግልፅ መወያየት ያለብን ግዜው አሁን ነው።
(ጸሐፊው በአውስትራሊያ ሜልቦርን ዲኪን ዩኒቨርሲቲ መምህር ሲሆኑ፣ በኢሜይል አድራሻቸው t.mekonnen@dekan.edu.au ማግኘት ይቻላል፡፡)
Via Ethiopian reporter
No comments:
Post a Comment