የእሁዱ ስብሰባና በኦነግ አመራር አባላት መካከል የተፈጠረው ተቃርኖ
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ሊቀ መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ከመኖሪያ ቤታቸው እንዳይወጡ ተደርገዋል የሚለውን ዜና ተከትሎ፤ በግንባሩ ጽሕፈት ቤት የተካሄደው የድርጅቱ አመራሮች ስብሰባ “ሊቀ መንበሩን ለማንሳት ነው” የሚል መረጃ እንዲሰራጭ ምክንያት ሆኖ ነበር።
ከዚህ በተጨማሪም የግንባሩ አመራር ለሁለት የመከፈሉ ጉዳይ መነጋገሪያ ከመሆኑ በተጨማሪ አቶ ዳውድ ኢብሳ ከሊቀ መንበርነታቸው ተነስተው በአቶ አራርሶ ቢቂላ እንዲተኩ ተደርጓል የሚል ወሬም በስፋት ሲነገር ቆይቷል።
ይሁን እንጂ አቶ ዳውድ ኢብሳን እንዲተኩ ተመርጠዋል የተባሉት አቶ አራርሶ ቢቂላ ዜናው ፍጽም ሐሰት ነው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አቶ አራርሶ ትናንት በኦነግ ጽሕፈት ቤት የተካሄደው ምርጫ የሊቀ መንበሩ አቶ ዳውድ ኢብሳ እውቅና የነበረው መሆኑን በመናገር አሁንም የድርጅቱ ሊቀ መንበር አቶ ዳውድ መሆናቸውን ገልጸዋል።
አቶ አራርሶ ስለ ስብሰባው እንደተናገሩት፤ በዋና አጀንዳነት “ሕዝቡ ምን አይነት ሁኔታ ውስጥ ይገኛል? ድርጅታችንስ ምን ድረጃ ላይ ነው? በተለይ ደግሞ ወደ አገር ከገባን በኋላ ምን አገኝን፣ ምን አጣን? የሚለውን ገምግመናል” በማለት ለቢቢሲ አብራርተዋል።
በተጨማሪም በአሁኑ ጊዜ በርካታ የግንባሩ አባላት እና አመራሮች መታሰራቸውን በተመለከተ የስብሰባው ተሳታፊዎች መወያየታቸውን አመልክተው “በዚህም ጉዳይ አንድ ሃሳብ ይዘን ተለያይተናል” ብለዋል።
ነገር ግን የግንባሩ ሊቀ መንበር በከተማው ውስጥ እያሉ፣ በሚመሩት ድርጅት ስብሰባ ላይ ሳይገኙ ውይይቱን ስለማድረጋቸውና አቶ ዳውድ ስለስብሰባው የሚያውቁት ነገር ስለመኖሩ ከቢቢሲ ለተጠየቁት ጥያቄ አቶ አራርሶ መልስ ሰጥተዋል።
“አቶ ዳውድ የተለየ ጉዳይ ስለገጠማቸው እየተንቀሳቀሱ የዕለተ ከዕለት ሥራቸውን ማከናወን አልቻሉም። ስለዚህም ስብሰባችን ላይ መገኘት አልቻሉም” ብለው፤ ይሁን እንጂ ስለ ጉዳዩ ከአቶ ዳውድ ጋር ተነጋግረውበት እንደነበር ገልጸዋል።
ጨምረውም፤ ስብሰባው እንዲካሄድ የሊቀ መንበሩን ይሁንታ እንዳገኙ በመጥቀስ “ውይይታችንን ሳንጨርስ ኔትዎርክ ተቋርጦ ነበር። ነገር ግን የድርጅቱ ከፍተኛ አመራር [ጉሚ ሰባ] ተሰብስቦ እንዲመክር ተስማምተን ነበር” ብለዋል።
ዋናው ሊቀ መንበር ባለመገኘታቸው በምክትሉ የሚመራ አይነት ሰብሰባ መካሄዱን በመግለጽ፤ በዚህም ሊቀ መንበሩን ጨምሮ “ምንም አይነት ሹም ሽር አልተካሄደም” ሲሉ አስረግጠው ተናግረዋል።
አቶ አራርሶ ቢቂላ ይህንን ይበሉ እንጂ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ገዳ ኦልጅራ (ዶ/ር) ግን የተካሄደውን ስብሰባ በተመለከተ የተለየ ሃሳብ እንዳላቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ትናንት በአቶ አራርሶ ቢቂላ የተመራው ሰብሰባ የድርጅቱ እውቅና የለውም” በማለት ስብሰባው በግንባሩም ሆነ በሊቀ መንበሩ የማይታወቅ መሆኑን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
አቶ አራርሶ፤ ከአቶ ዳውድ ስብሰባ ለማካሄድ ፍቃድ እንደተሰጣቸው ተናግረው ስብሰባ ሲጠሩ፤ ገዳ (ዶ/ር) ወደ አቶ ዳውድ እንደደወሉና፤ አቶ ዳውድ ስለ ስብሰባው መረጃ እንዳልደረሳቸው እንደገለጹላቸው ተናግረዋል።
ያለ ድርጅቱ ሊቀ መንበር እውቅና ስብሰባ ማካሄድ ተገቢ አይደለም ብለው ለስብሰባ የሄዱ ሰዎችን እንደከለከሉ ገልጸው፤ “ሲከለከሉ የታጠቁ የመንግሥት አካላትን ይዘው መጥተው፣ በጉልበት ገብተው ነው ስብሰባቸውን ያካሄዱት። ስብሰባው ሕጋዊ አልነበረም” ብለዋል።
ገዳ (ዶ/ር) አያይዘውም ስብሰባው ላይ የተነሱ አጀንዳዎችን እንደማያውቁ ተናግረዋል።
በስብሰባው ሹም ሽር ተካሂዶ፤ በአቶ ዳውድ ምትክ አቶ አራርሶ ሊቀ መንበር ሆነዋል የሚል ወሬ እንደተናፈሰ ጠቅሰን፤ እውነት ስለመሆኑ ሲጠየቁም እሳቸውም ተጨባጭ መረጃ እንዳልደረሳቸው አስረግጠው፤ “ከወሬ ያለፈ አይመስለኝም። ለዚያ የሚያበቃ ስብሰባ አይደለም” ብለው ምላሽ ሰጥተዋል።
ቢቢሲ ካናገራቸው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አመራር አባላት በተጨማሪ ለተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ስለተፈጠረው ነገር የሚሰጡት ማብራሪያ እርስ በርሱ የሚቃረን ሲሆን ግለሰቦች ከሚሰጡት ምላሽ ውጪ እስካሁን ከግንባሩ ተሰጠ መግለጫ የለም።
ሊቀመንበሩ ከአቶ ዳውድ ኢብሳ ከመኖሪያቸው መውጣት እንዳልቻሉ እንዲሁም የስልክ ግንኙነት ስለሌላቸው በድርጅቱ ውስጥ እተካሄደ ስላለው ነገር ቁርጥ ያለ ነገር ለመስማት አልተቻለም።
No comments:
Post a Comment